FDRE Ministry of Agriculture

የዲጂታል ግብርና ፍኖተ-ካርታ የአርሶናአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው፡- ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)

ግብርና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲዩት እና ከጌትስ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ዲጂታል ግብርና ፍኖተ ካርታ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የግሉ ዘርፍ እና የልማት አጋር ድርጅት ተወካዮች በተገኙበት ይፋ ተደርጓል፡፡

(አዲስ አበባ፣ ጥር 27 ቀን 2017 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር)

የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ዲጅታል ግብርና ፍኖተ ካርታ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን እና ገበያ ተኮር ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ጉልህ ሚና የሚጫወት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ፍኖተ ካርታው የግብርና ግብዓት ተደራሽነትን ለመከታተል እና ለማስተባበር ያለውን ፋይዳም የላቀ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ፍኖተ ካርታው የግብርና ፋይናንስ ተደራሽነትን የሚያቀላጥፍ እና የአርሶ/አርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ ፍኖተ ካርታው ከቀበሌ እስከ ፌደራል ያለው መረጃ በአንድ ቋት ማግኘት የሚያስችልና መረጃዎቹም ተናባቢ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የዲጅታል ግብርና ፍኖተ ካርታን በማዘጋጀት ሂደት ውስጥ የበኩላቸውን ድርሻ ለተወጡት የልማት አጋር ድርጅቶች፣ መንግስታዊ ላልሆኑ አካላት እና ለግሉ ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ምስጋናም አቅርበው፣ ለፍኖተ ካርታው ተፈፃሚነት ባለድርሻ አካላት በቀጣይም ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጎን በመቆም የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በበኩላቸው የግብርናው ዘርፍ ለሀገር ኢኮኖሚ እና ለዜጎች መተዳደሪያ መሆኑን አንስተው፣ ፍኖተ ካርታው የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ ያለው አበርክቶ የላቀ ነው ብለዋል፡፡

የግብርና ግብዓት መጓደል፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ድርቅ እና ደካማ የገበያ ትስስር የግብርናው ዘርፍ ተግዳሮቶች መሆናቸውን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ ትክክለኛ መረጃዎችን ለአርሶ/አርብቶ አደሩ በማድረስ በዘርፉ ያሉትን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ የዲጅታል ግብርና አስፈላጊነትን አብራርተዋል፡፡

የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲዩት ዳይሬክተር ጄኔራል ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) አርሶ/አርብቶ አደሩ ከማምረት እስከ ገበያ ባለው እሴት ሰንሰለት ለረጅም ዓመታት በሰው ኃይል ይሰራ እንደነበርና በዚህም አርሶና አርብቶ አደሩ ተገቢውን መረጃ ባለማግኘቱ ተጠቃሚነቱ አናሳ መሆኑን አስታውሰው፣ ዲጅታል ግብርናው አርሶ/አርብቶ አደሩ መረጃና የልፋቱን ዋጋ እንዲያገኝ የሚያስችል መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

በመድረኩ የፍኖተ ካርታው አስፈላጊነት ላይ የፓናል ውይይት የተደረገ ሲሆን ፍኖተ ካርታው የሚተገበረው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2025 እስከ 2032 ነው፡፡

ዘጋቢ፡- ዮሐንስ ደመቀ

ፎቶግራፍ፡- ጌታቸው ምትኩ

#ከማምረትበላይ

#BeyondProduction

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *