FDRE Ministry of Agriculture

የዲጂታል ኤክስቴንሽን አገልግሎትን በማጎልበት የወተት ምርታማነትን ማሳደግ!

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14/2019 (ግብርና ሚኒስቴር) የወተት ምርታማነትን ለማሳደግ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ የኤክስቴንሽን አገልግሎት ዙሪያ ከክልሎች ለተውጣጡ ለእንስሳት እርባታ ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጥቷል።

በተዘጋጀው የሥልጠና መድረክ ላይ የእንስሳትና ዓሳ ኤክስቴንሽን መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መላከ አሰፋ ቀደም ሲል የነበረው ማንዋል የኤክሰቴንሽን አገልግሎት አሰጣጥ አድካሚና ጊዜ የሚወስድ ከመሆኑም ባሻገር ለሁሉም አርሶ እና አርብቶ አደር በወቅቱ ተደራሽ ለማድረግ አስቸጋሪ እንደነበር አስታውሰው፣ ችግሩን ለመቅረፍ አሰራሩን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘመናዊ የማድረግ ስራዎች በመሰራት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት እና ዓሣ ሀብት ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ አዚዝ አያሌው በበኩላቸው ከ“SNV” ብሪጅ ፕላስ ፕሮጀክት ጋር በመተባበር የወተት ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ጠንካራ መሰረቶች እየተጣሉ ናቸው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ላም-ተኮር የምክር አገልግሎቶችን፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን፣ የገበያ ትስስርን እና የአርሶ አደሮችን አቅም ማጎልበት ስራዎችን በአንድ ላይ በማቀናጀት የወተት ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግ እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ አቶ አዚዝ ገልጸዋል።

በስልጠና መድረኩ ላይ እንደተገለፀው በዲጂታል ፕላትፎረሙ በአማርኛ፣ በኦሮምኛ እና በትግርኛ ቋንቋዎች የተላለፉ የወተት ላም-ተኮር የአርሶ አደሮች የድምፅ፣ የምስለ-ድምጽና የጽሁፍ መልዕክት አገልግሎቶች ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገቡ ይገኛሉ። እስካሁን ከ65 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እና ከ2 ሺህ በላይ የልማት ጣቢያ ሰራተኞች ተደራሽ ሆነዋል፤ የድምፅ መልእክቱን የመቀበል ምጣኔም በአርሶ አደሮች 65 በመቶ እንዲሁም በልማት ጣቢያ ሰራተኞች 78 በመቶ ደርሷል።