FDRE Ministry of Agriculture

የዱረም ስንዴ ልማት የፓስታና መኮረኒ ፋብሪካዎችን ፍጆታ ለማሟላት!

ቢሾፍቱ፣ ግንቦት 1/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) የአየር ንብረት የሚቋቋም ስንዴ እሴት ሰንሰለት ልማት ፕሮጀክት በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሶማሌና አፋር ክልሎች ከ20 ዞኖች በ76 ወረዳዎች ውስጥ 800 ሺ አርሶአደሮችን አቅፎ እየሰራ ነው።

ፕሮጀክቱ ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በየጊዜው እየተለወጠ የመጣውን የአየር ንብረት ሊቋቋሙ የሚችሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማውጣት ለአርሶአደሩ የማስተዋውቅና የማባዛት ሥራ እየሰራ ይገኛል።

የፕሮጀክቱ ብሔራዊ አስተባባሪ አብዱልሰመድ አብዶ እንደ ዱረም ስንዴ ያሉ የአየር ንብረት መቋቋም የሚችሉ የዘር ዝርያዎችን ማውጣት፣ የአፈር ለምነትንና ጤንነትን ማሻሻል፣ የመስኖ ልማትና መካናይዜሽን ላይ ፕሮጀክቱ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

አምና 2,289 ፓምፖችን ለአርሶአደሮች ያሰራጨ ሲሆን ዘንድሮም 300 ሶላር ፖምፖችን ለማሰራጨት እየሰራ መሆኑን የገለጹት አስተባባሪው፣ ፕሮጀክቱ 18 የመስኖ ተቋማትንም እያስገነባ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ እንደየሥነ-ምህዳሩ ተስማሚ የዝርያ አማራጮችን እያቀረበ ሲሆን አምና 16 በምርምር የተገኙ ዝርያዎች ውጤታማነታቸው ተረጋግጠው አርሶአደሩ ዘንድ ደርሰዋል።

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሰብል ልማት ዳይሬክተር ዶ/ር ፍቃዱ ጉርሙ እንደገለጹት በሽታን መቋቋም የሚችሉ የስንዴ ዝርያዎችን የማፍለቅ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

ባለፈው ዓመት 4 የዳቦ ስንዴ ዝርያዎች የተለቀቁ ሲሆን አሁን ደግሞ የዱረም ስንዴ ዝርያን በማስፋፋት ከውጭ የሚገባውን የፓስታና መኮረኒ ስንዴን ለማስቀረት እየተሰራ መሆኑን ዶ/ር ፍቃዱ ተናግረዋል።

በቢሾፍቱ ግብርና ምርምር ማዕከል የዱረም ስንዴ ከፍተኛ ተመራማሪ ዶ/ር አለማየሁ ዘመዴ በምርምር ማዕከሉ እየተባዛ ያለው የዱረም ስንዴ (ኡቱባ) በሄክታር ከ50 እስከ 55 ኩንታል ምርት እንደሚገኝ አብራርተዋል።

የዱረም ስንዴን ተመራጭ የሚያደርገው በመስኖ ሲለማ በዝናብ ከሚለማው የተሻለ ምርት መስጠቱ፣ በሽታና ተባይ የሚቋቋም መሆኑና ለፓስታና መኮረኒ ፋብሪካዎች ፍጆታ ምቹ መሆኑ ነው።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የዱረም ስንዴ ልማትን እየሰራ ያለው የቢሾፍቱ ግብርና ምርምር ማዕከል ሲሆን የዳቦ ስንዴ ልማት ማሻሻያ ፕሮግራምን የሚያከናውነው የቁልምሳ ግብርና ምርምር ማዕከል ነው።

ዘጋቢ፦ ባህሩ ሰጠኝ

ፎቶ፦ ማቲዎስ ተገኝ