አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29/ 2018 (ግብርና ሚኒስቴር) የናይጄሪያ ልዑካን የጥናት ቡድን አባላላት በደቡብ-ደቡብ የመማማር መርህ መሰረት ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብት ልማት ያካበተችውን ተግባራዊ ልምድ በመመልከትና በመለዋወጥ ለናይጄሪያ የሚጠቅሙ ተሞክሮዎችን ለመውሰድ እንዲሁም ትብብርን ለማጠናከር የሚያግዝ ጥናታዊ ጉብኝት አደረጉ፡፡
የ”ደቡብ-ደቡብ ልምድ ልውውጥ” በተመሳሳይ ልማት ውስጥ ያሉ አገሮች ልምድ፣ እውቀት፣ ቴክኖሎጂ፣ ፖሊሲና አሠራሮቻቸውን በመለዋወጥ እርስ በእርስ መማማር የሚቻልበት መድረክ ነው።

በግብርና ሚኒስቴርና አግሪ ከርቭ ኢትዮጵያ ትብብር ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፍ ያላትን ተሞክሮ ከናይጄሪያ ለመጡ በእንስሳት ዘርፍ የሚሰሩ ከፍተኛ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት እንዲሁም በእንስሳት ልማት፣ በእንስሳት ጤና እና ኤክስቴንሽን አገልግሎት፣ በምርምር፣ አግሪቢዝነስ፣ ኢንቨስትመንት፣ ህብረት ሥራ ማህበራት፣ ማቀነባበር እና ገበያ ላይ ፍላጎትና ኃላፊነት ላላቸው የዘርፉ ባለሙያዎች እና ለባለድርሻ አካላት ገለጻ ተደርጎላቸዋል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ደጀኔ ታከለ ኢትዮጵያና ናይጀሪያ ለበርካታ አመታት በዘርፈ-ብዙ ጉዳዮች ጠንካራ ግንኙነት የፈጠሩ መሆናቸውንና ሀገራቱ በግብርናው ዘርፍ ያላቸውን ተሞክሮ፣ ፈጠራ፣ ስኬትና ትምህርት የሚለዋወጡበት መድረክ እየሰፋ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የጀመረችው የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ ለእንስሳት ዘርፉ ምርታማነት እድገት ትልቅ ሚና መወጣቱን አቶ ደጀኔ ገልፀው በዝርያ ማሻሻል፣ በግብዓት ስርጭት፣ በመኖ ልማትና እንስሳት ጤና ላይ ሰፊ ስራ መሰራቱን ለልዑካን ቡድኑ አብራርተዋል፡፡
ኢኒሼቲቩ የእንስሳት ምርታማነትን በማሳደግ የምግብና ስነ-ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ ከውጭ የሚገቡ የግብርና ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች በመተካት፣ የኤክስፖርት ምርትን በማሳደግና ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም አማካሪው ለልዑካን ቡድኑ ገልፀዋል፡፡
የልዑካን ቡድኑ አባላት በኢትዮጵያ የዘርፉን ተቋማት በመጎብኘት ባደረጉት የልምድ ልውውጥ በእንስሳት ምርት፣ በእንስሳት ሕክምና እና በኤክስቴንሽን አገልግሎቶች፣ በግብርና ንግድ፣ በማቀነባበርና በገበያ ልማት፣ በኢንቨስትመንት እና በእሴት ሰንሰለት፣ በፖሊሲና ስትራቴጂዎች ላይ ልምዶችን በጥልቀት ለማየት ዕድል ፈጥሮላቸዋል።
እነዚህ ልምዶች ወደፊት የኢትዮጵያ እና የናይጀሪያ ተቋማት ጠንካራ ትብብር እንዲፈጥሩ ያስችላሉ፡፡
