የከተማ ግብርና ከለውጥ ወዲህ መንግስት በሰጠው ትኩረት በዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂ ታግዞ አበረታች ውጤቶችን አስመዝግቧል፡፡ የከተማው ነዋሪዎች ጥራት ያለው ምርት በማምረት ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ፣ በርካታ የስራ ዕድሎች እንዲፈጠሩ፣ የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ እና ገባያ እንዲረጋጋ የበኩሉን አስተዋፅዖ አበርክተዋል፡፡
በየነዋሪው ጓሮ፣ በየሴክተሩ፣ በየትምህርትና ጤና ተቋማት እንዲሁም በሌሎች ድርጅቶች ተጀምሮ በኢኮኖሚው ዘርፍ ውስጥ የራሱን አሻራ እያኖረ ያለውን የከተማ ግብርና ስራን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የዝናብ ውሃን ለመስኖ መጠቀም ይገባል፡፡
የዝናብ ውሃን ከጣሪያ፣ ከጠንካራ መሬት እና ከሌሎች ተስማሚ ምንጮች በመሰብሰብ በታንከር/በትላልቅ ሮቶዎች ውስጥ በማጠራቀም በበጋ ወቅት ለከተማ ግብርና መስኖ መጠቀም ያስፈልጋል።
የዝናብ ውሃን አጠራቅሞ መጠቀም የውሃ እጥረትን በመቀነስ፣ የከተማ ውሃን በመቆጠብ፣ በበጋ ወቅት ለመስኖ በመዋል እና የጎርፍ አደጋን በመቀነስ ዘረፈ-ብዙ ፋይዳ አለው።
የዝናብ ውሃ በሚሰበሰብበት ጊዜ በጣሪያው ላይ የተከማቸ አቧራ፣ ቆሻሻና ሌሎች በካይ ነገሮች ወደ ማጠራቀሚያው እንዳይገቡ የመጀመሪያውን የዝናብ ውሃ ማስወገድ እና ቀጥሎ የሚመጣውን ውሃ ማጣራትና ማጠራቀም ይገባል።
የሚሰበሰበው የዝናብ ውሃ መጠን ሚወሰነው በዝናብ መጠን፣ በጣሪያው ስፋት እና ማጠራቀሚያው ባለው ስፋት ነው። የጣሪያውን ስፋት ርዝመቱን በወርዱ በማባዛት ማስላት ይቻላል። በመሆኑም የዝናብ መጠን በበዛ፣ ጣሪያው በሰፋ እና ማጠራቀሚያው በተሻለ ቁጥር የሚሰበሰበው የውሃ መጠን ይጨምራል።

የማጠራቀሚያና የጥራት አስተዳደር
የተሰበሰበው ውሃ በንፁህና በተሸፈነ ማጠራቀሚያ መቀመጥ አለበት፡፡
➜ ከብክለት መጠበቅና በአግባቡ መጠቀም ይገባል።
➜ ታንከሩ ከፀሐይ፣ ከቆሻሻ እና ከአይጥ/ነፍሳት የተጠበቀ መሆን አለበት።
➜ ታንከሩን በየጊዜው ማጽዳት።
➜ የመስኖ መስመር እንዳይዘጋ ማጣሪያ መጠቀም ያስፈልጋል።
➜ ለሚበሉ አትክልቶች የተበከለ ወይም ያልታከመ ቆሻሻ ውሃ ከመጠቀም መቆጠብ ተገቢ ነው።
የተጠራቀመወን የዝናብ ውሃን በመስኖ ቴክኖሎጂዎች መጠቀም
ሀ. ቀላል የመስኖ ሶላር ፓምፕ መጠቀም፡- ይህ ቴክኖሎጂ ለአነስተኛ የከተማ ማሳ ወይም ጓሮ የሚውል ነው።
ለ. ዘመናዊ የመስኖ ሶላር ፓምፕ መጠቀም፡- ይህ ቴክኖሎጂ ውሃን በቀጥታ ወደ ሰብል ሥር የሚያደርስ ሲሆን ታዳሽ ኃይልን በመጠቀም በበጋ ወቅት የተጠራቀመውን ውሃ ከማጠራቀሚያው ወደ ማሳ ለማድረስ የሶላር ፓምፕ መጠቀም በጣም ተስማሚ ነው፡፡ ለዚህም የጠብታ መስኖን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል።
የጠብታ መስኖ ዋና ዋና ጥቅሞች
➜ የውሃ ብክነት ዝቅተኛ ነው፡፡
➜ ውሃው በቀጥታ ወደ ሥር ይደርሳል፡፡
➜ ከፍተኛ የመስኖ ቅልጥፍና አለው፡፡
➜ የሰብል ምርታማነት ለማሻሻል ይረዳል፡፡
➜ የውሃ እጥረት ላላቸው የከተማ አካባቢዎች ተስማሚ ነው፡፡
ስለዚህ የከተማ ነዋሪው በክረምት ወቅት የሚባክነውን የዝናብ ውሃን በማጠራቀም በበጋ ወቅት ለመስኖ በመጠቀም የተለያዩ አትክልቶችን እና ፍራፍሬዎችን በሚመቸው መንገድ ማልማት ይችላል፡፡
