FDRE Ministry of Agriculture

የዘር ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተቋቋመው የኢትዮጵያ የማህበረሰብ ዘር ባንኮች ኔትወርክ

(ቢሾፍቱ፣ ታኅሳስ 9 ቀን 2018፣ ግብርና ሚኒስቴር)

በኢትዮጵያ 53 የማህበረሰብ የዘር ባንኮች ያሉ ሲሆን ባንኮቹ ከ10 ሺ 7 መቶ በላይ አርሶአደሮችን ተጠቃሚ አድርገዋል።

ጥራቱና ደህንነቱ የተጠበቀ ዘር ለአርሶአደሩ ተደራሽ ለማድረግ ያሉትን የዘር ባንኮችን ማጠናከር እና አዳዲስ  ባንኮችን መመስራት ይገባል።

በሀገራችን ባሉት የማህበረሰብ የዘር ባንኮች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር “የኢትዮጵያ የማህበረሰብ ዘር ባንኮች ኔትወርክ” ተመስርቷል።

የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ካርታ ካስኬ የኢትዮጵያ የማህበረሰብ ዘር ባንኮች ኔትወርክ የዘር ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

ይህ ኔትወርክ የማህበረሰብ ዘር ባንኮች እንዲተዋወቁና ልምድ እንዲለዋወጡ ብሎም ማህበረሰቡ ዘር እራሱ እንዲያዳቅልና መረጃ እንዲለዋወጥ መልካም አጋጣሚዎችን የሚፈጥር መሆኑን ዶ/ር ካርታ ጠቁመዋል።

ከምርምር ተቋማትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን የዘረ መል ሀብት ለማሻሻል

በቴክኖሎጂ በመደገፍ እየተሰራ ነውም ብለዋል ዶ/ር ካርታ።

የአካባቢ፣ ብዝሀ ሕይወትና የአየር ንብረት ለውጥ ፎረም ዳይሬክተር ዶ/ር ግርማ ባልቻ የተቋቋመው ኔትወርክ የኢትዮጵያን የአዝርዕት ዝርያ ተንከባክቦ ለማቆየት ያግዛል ሲሉ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ያሉት 53 የማህበረሰብ የዘር ባንኮች በቂ አለመሆናቸውን ዶ/ር ግርማ ገልጸው ቁጥራቸውን እስከ 2 መቶ ማድረስ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የማህበረሰብ ዘር ባንኮች ኔትወርክ ለአርሶአደሮች፣ ግብርና ሴክተሮች፣ የምርምር ተቋማት፣ የልማት ድርጅቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት አገናኝ ድልድይ ሆኖ ያገለግላል።

የዘር ባንኮች ነባር የአርሶአደር የአዝዕርት ዝርያዎችን ለመጠበቅና በዘላቂነት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማድረግ የተቋቋሙ ናቸው።

የማህበረሰብ ዘር ባንኮች ስኬትና ተግዳሮት፣ የባለድርሻ አካላት ሚና እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል ።

ዘጋቢ፦ ባህሩ ሰጠኝ

ፎቶግራፈር፦ ጌታቸው ምትኩ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *