FDRE Ministry of Agriculture

የዘመነ የእንስሳት ጤና መረጃ ስርዓት ለውጤታማ የበሽታ መከላከል እና ቁጥጥር

/አዳማ፣ የካቲት 6 ግን 2018 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር/

ብሔራዊ የእንስሳት ጤና መረጃ ስርዓት (NAHIS-DHIS2) ለመገንባት ያለመ የስርዓቱ ዝርዝር መስፈርት እና መለኪያዎች (System Requirement Specification/SRS) ላይ ከፌዴራል፣ ከክልል ግብርና ቢሮ እና ከእንስሳት ጤና ላቦራቶሪዎች፣ ከFAO, HISP Ethiopia, Project HOPE የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት እየተወያዩ ይገኛሉ።

ግብርና ሚኒስቴር መረጃ ላይ በተመሰረተ ውሳኔ ለመስጠት፣ በሽታ ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እንዲሁም ዓለም አቀፍ ግዴታን በመወጣት የውጭ ንግዱን ለማሳለጥ የሚረዱ በተንቀሳቃሽ ስልክ እና በድረ-ገጽ የታገዙ የበሽታ ክስተት የማሳወቂያ (Animal Disease Notification and Investigation System (ADNIS) እና ወርሃዊ የበሽታ እና ክትባት ሥራዎች ሪፖርት ማድረግያ ስርዓቶችን (Disease Outbreak and Vaccination Activity Reporting (DOVAR-II) በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል፡፡

በስርዓቶቹ ላይ የሚስተዋሉ ክፍቶችን በመሙላት እና ተጨማሪ መረጃዎች መሰብሰብ እና ማደራጀት እንዲቻል ከዓለም እርሻ ድርጅት (FAO) ጋር በመተባበር ሁሉን አቀፍ የእንስሳት ጤና መረጃ ስርዓት (NAHIS) በ DHIS2 በመታገዝ ለማልማት ከኦስሎ ዩኒቨርሲቲ/HISP Ethiopia/ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈርሞ ወደ ሥራ ተገብቷል።

የመረጃ ስርዓቱን ለማልማት አስፈላጊ የሆነው የስርዓቱ ዝርዝር መስፈርቶች እና መለኪየዎች (System Requirement Specification) የሚገልጽ ሰነድ የተዘጋጀ ሲሆን የክልል የእንስሳት ጤና አገልግሎት አስተባባሪዎች፣ የእንስሳት ጤና ላቦራቶሪ ኃላፊዎች፣ ኤፒዴሚዮሎጂ እና የ ICT ባለሙያዎች፣ FAO, Project Hope, aLIVE project እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ሰነዱን ለማዳበርና ከአገሪቱ የእንስሳት ጤና አግልግሎት ነባራዊ ሁኔታ እና ከዓለም አቀፍ መስፈርቶች ጋር ለማጣጣም ውይይት እየተደረገ ነው።

በመድረኩ በሚ/ር መ/ቤቱ በእንስሳት ዓሳ ሃብት ልማት ዘርፍ በእንስሳት ጤና እና ቬተርነሪ ፐብሊክ ሄልዝ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ስር የኢፒዲሞሎጂ ዴስክ ሃላፊ ዶ/ር ካሰው አምሳሉ፣ NAHIS-DHIS2 መተግበር የበሽታ ወረርሽኝ ከመከሰቱ በፊት ቀድሞ ለመከላከልና ለድንገተኛ አደጋዎች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው እና በሽታ ሲከስት ፈጥኖ ለይቶ በማሳወቅ ምላሽ እንዲሰጥ የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡



ከዚህ በተጨማሪ አዲስ የሚገነባው የመረጃ ስርዓት በፊት ያልተካተቱ የእንስሳት ጤና መረጃዎችን ማካተት በመቻሉ በተሟላ መረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ለመስጠት ያስችላል፡፡ ይህም የመረጃ መቆራረጥን የስርዓቶችን አለመናበብ በማስቀረት የሀገሪቱን የእንስሳት ጤና በተሻለ መንገድ ለመጠበቅ እንደሚረዳ ገልጸዋል።

ሥርዓቱ የእንስሳት የውጭ ንግዱን የሚያስተጓጉሉ የድንበር ዘለል እና ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ (Zoonotic) እንዲሁም በየወቅቱ የሚከሰቱ አዳዲስ በሽታዎችን ክስተትና ስርጨት ስትራቴጂክ በሆነ መንገድ ለመግታት የሚያስችል ትልቅ አቅም እንዳለው ኃላፊው አስረድተዋል።

በ FAO ኢትዮጵያ የድንበር ዘለል በሽታዎች የአደጋ ምላሽ ማዕከል (FAO ECTAD) ምክትል ቡድን መሪ ዶ/ር ጌታቸው ጋር በበኩላቸው የቴክኖሎጂ ሽግግሩ እና የመረጃ ስርዓት ማጠናከሩ ከወረዳ እስከ ፌዴራል ደረጃ ያለውን የመረጃ ፍሰት ግልጽና የተሳለጠ በማድረግ ውሳኔ ሰጪዎች በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርተው የተቀናጀ እርምጃ እንዲወስዱ የሚያግዝ መሆኑን አስረድቷል፡፡

ይህ ቴክኖሎጂ የሀገሪቱን የእንስሳት በሽታ አሰሳና የመረጃ ልውውጥ ከዓለም አቀፍ የእንስሳት ጤና ድርጅት (WOAH) መመዘኛዎች ጋር የሚያጣጥም መሆኑንም አብራርቷል፡፡

በአጠቃላይ ይህ የስርዓቱ ዝርዝር መስፈርቶች እና መለኪየዎች በጋራ ታይቶ ስርዓቱ ሲለማ የአገሪቱን ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነውን የእንስሳት ሀብት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ የላቀ ሚና ይጫወታል።

ይህም የመረጃ ወቅቱን የጠበቀ እና ተደራሽ እንዲሆን የሚያደረግ በመሆኑ የመረጃ መቆራረጥን በማስቀረት የሀገሪቱን የእንስሳት ጤና ለማሻሻል እና በሽታዎችን በተሻለ መንገድ ለመቆጣጠር ይረዳል።

ለተከታታይ ሦስት ቀናት በሚቆየው በዚህ መድረክ የስርዓቱ ዝርዝር መስፈርቶች እና መለኪየዎች ሰነድ በሰፊው ውይይት ተደርጎበት እንዲዳብር በማድረግ ፀድቆ የስርዓት ማበልፀግ ሂደቱ የሚጀመር ይሆናል፡፡

ዘጋቢ፡-ጌዲዮን ነጋሸ
ፎቶግራፈር፡-ዮዲት እንዳለው

#ከማምረትበላይ
#BeyondProduction