ቢሾፍቱ፣ ነሐሴ 26/2018፣ (ግብርና ሚኒስቴር) በግብርና ሚኒስቴር እና በኔዘርላንድ የልማት ድርጅት (SNV) ትብብር የወተት ላሞችን ዝርያ መለየት፣ የመረጃ ስርዓት ውስጥ ማስገባት እና መለያ መስጠት ላይ ያተኮረ ስልጠና እየተሰጠ ነው፡፡
በስልጠናው ከአዲስ አበባ፣ ከሸገር ከተማ አስተዳደር፣ ከኦሮሚያ እና ከአማራ ክልሎች የተውጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ የባንክ ተወካዮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት ጤና እና ቬተርነሪ ፕብሊክ ሄልዝ መሪ ስራ አስፈጻሚ ሲሳይ ጌታቸው (ዶ/ር) ለእንስሳት ምርትና ምርታማነት የዘመነ የመረጃ ስርዓት መኖር ወሳኝ መሆኑን ገልፀው የእንሰሳት እርባታ ዘርፍ በዘመናዊ የመረጃ ስርዓት መመራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
በስልጠናው ሰልጣኞቹ በንድፈ ሀሳብና በተግባር የታገዘ ስልጠና የሚሰጣቸው መሆኑን እና ወደ መጡበት ሲመለሱ ለ15 ቀናት ስልጠናውን በተገባር እንዲያዳብሩት ይደረጋል በማለት ዶ/ር ሲሳይ አስረድተዋል፡፡
የእንስሳትን መረጃ አደራጅቶ በመያዝ ለበሽታ ቁጥጥር፣ ለዝርያ ልየታ፣ ለምግብ ደህንነትና ለወጪ ንግድ ምቹ መደላድል እንደሚፈጥር በስልጠናው ወቅት ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም የእንስሳት ባለንብረቶች መረጃውን በማሟላታቸው ከባንኮችና አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት የብድር አገልግሎት በተሻለ ሁኔታ የማግኘት እድል እንዳላቸው ከተለያዩ ተቋማት በመጡ የባንክ ተወካዮች ገለፃ ተደርጓል፡፡
