ግብርና ሚኒስቴር ባለፉት አራት ዓመታት የእንስሳት መኖ ምርታማነትን ለማሳደግና የአርሶአደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተከታታይነት ያላቸው አበረታች ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።

በተሻሻሉ መኖ ዝርያዎች፣ በተፈጥሮ ግጦሽ አያያዝ እና በሰብል ተረፈ ምርት አጠቃቀም ዙሪያ በተከናወኑ ሰፊ ተግባራት በመኖ ልማት ዘርፉ ላይ በየደረጃው ለውጥ ማምጣት ተችሏል።

በተቀናጀ ጥረት የዘርፉ ተደራሽነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ የመጣ ሲሆን የተጠቃሚ አርሶአደሮች፣ ሴቶችና የወጣቶች ቁጥር ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ወደ 3 ነጥብ 1 ሚሊዮን ከፍ ብሏል፡፡ ከተፈጥሮ ግጦሽ፣ ከሰብል ተረፈ ምርት፣ ከኢንዱስትሪና ከተሻሻሉ የመኖ ዕፅዋት የሚሰበሰበው ዓመታዊ ድርቆ መኖ 250 ሚሊዮን ቶን ደርሷል።

በተለይም የሰብል ተረፈ ምርትን በተገቢው መንገድ በማሰባሰብና የተፈጥሮ ግጦሽ ማሻሻያ ስትራቴጂዎችን በመተግበር ረገድ የተከናወኑት ስራዎች ለጠቅላላ ምርቱ ዕድገት ትልቁን ድርሻ አበርክተዋል።

የተሻሻለ መኖን በፓኬጅ ማልማት፣ የግልና የወል ግጦሽ መሬቶችን በተሻለ ዘዴ መንከባከብ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ተረፈ ምርቶችን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል መቻሉ የአርሶአደሩን የመኖ እጥረት በዘላቂነት ለመቅረፍ ትልቅ እገዛ አድርጓል።

ጥራት ያላቸው የተሻሻሉ የመኖ ዘሮች አቅርቦትን በከፍተኛ ደረጃ ከማሳደግ ጎን ለጎን፣ በሁሉም ስነ-ምህዳር ውስጥ በመስኖ መኖን የማልማት ተግባር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል። በዚህም በመስኖ የሚለማውን የመኖ መሬት ስፋት ወደ 52 ሺህ 100 ሄክታር ከፍ ማድረግ የተቻለ ሲሆን ይህም የዘርፉን ቀጣይነት አስተማማኝ ያደርገዋል።
በአጠቃላይ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና አርሶ አደሮች ተቀናጅተው በቁርጠኝነት በመስራታቸው ይህ ስኬት ተመዝግቧል።
አዘጋጅ፦ ባህሩ ሰጠኝ
