ጅማ፣ መስከረም 10/2019 (ግብርና ሚኒስቴር) በስፓኒሽ ኮኦፕሬሽን ፕሮጀክት በጀት ድጋፍ በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ቀርሳ ወረዳ በቶሊ ቀርሱ ቀበሌ በቴክኖሎጂ ተደግፎ የተሰራው የሙሉ ዓሳ ግብርና (የአኳካልቸር) ሰርቶ ማሳያ ለአሚኖና ቢያ የዓሳ እርባታ ማህበር የማስረከቢያ ስነ-ስርዓት ተከናውኗል፡፡
በሀገራችን ያሉትን የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ የውሃ አካላትን ተጠቅሞ ዘርፉን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ሲሆን እንደ ሀገር እየተስፋፋ ያለው የዓሳ ግብርና (የኩሬ ዓሳ እርባታ) ለዚህ ማሳያ ነው፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት እና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ አማካሪ ወ/ሮ ፅጌረዳ ፍቃዱ የምግብና ስርዓተ-ምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የዓሳ ግብርና የጎላ ሚና ስላለው የውሃ አማራጮች ባሉበት አካባቢ ሁሉ ለማህበረሰቡ ተደራሽ ይደረጋል ብለዋል፡፡
ስራው ትብብርን የሚጠይቅ በመሆኑ የተጀመረው ትብብር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡
የእንስሳት እና ዓሣ ሀብት ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ አዝዝ አያሌው በአካልም ሆነ በአእምሮ የተሟላ ዜጋን ለማፍራት ዓሳ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ጠቅሰው፣ አካባቢው ምቹ ስለሆነ የተጀመረውን ስራ በማስፋፋት በአካባቢው የዓሳ ክላስተር ለመፍጠር መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
እንደ ሀገር አንድ ዓይነት ፆታ ያላቸውን የቆሮሶ ዝሪያ ዓሳ ማስፈልፈያና ማባዣ ቴክኖሎጂ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ የተደረገው በዚህ በቶሊ ቀርሱ ቀበሌ ነው ያሉት የዓሣ ሀብት ልማት ዴስክ ኃላፊ ዶ/ር ፋሲል ዳዊት፣ በቦታው ላይ ያሉት ኩሬዎችም በሳይንሱ መሰረት የራሳቸው ስራ እንዳላቸው አብራርተዋል፡፡
የቀርሳ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሃሚድ አባፋጂ በበኩላቸው ወረዳው ለዓሳ እርባታው ያለውን ምቹ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት የተጀመረውን ስራ ለማስፋፋት፣ ገበያን ለማስተሳሰር እና ሰፊ የስራ ዕድል ለመፍጠር በዕቅድ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የአሚኖና ቢያ የዓሳ እርባታ ማህበር የዓሳ ምርቱን ለገበያ ለማቅረብ ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል፡፡
