FDRE Ministry of Agriculture

የዓሳ ግብርናን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ማድረግ የምግብና ስርዓተ-ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ!

እንደ ሀገር ባለን የዓሳ አቅም ልክ እንዳንጠቀም ወደኋላ የጎተቱን ማነቆዎችን ለይቶ ለመፍታት በተዘጋጀው  የዓሳ ሀብት  ፍኖተ-ካርታው በዓሳ ግብርና  ብቻ በ10 ዓመት ውስጥ 402 ሺህ ቶን የዓሳ ስጋ ማምረት እንደሚቻል የተቀመጠ ሲሆን ይህም ሀገራችን በዓሳ ግብርና (በአኳካልቸር) ከፍተኛ አቅም እንዳላት አመላካች ነው፡፡

ዓሳ ባለው በምግብ ንጥረ-ነገር ይዘቱ የምግብና ስርዓተ-ምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የጎላ ሚና አለው፡፡  በአካልም ሆነ በአእምሮ የተሟላ ጤናማ ዜጋን ለማፍራት ዓሳ ያለውን ፋይዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት የውሃ አማራጮች ባሉበት አካባቢ ሁሉ የዓሳ ግብርናን ለማህበረሰቡ ተደራሽ የማድረግ ስራ በትኩረት እየተከናወነ ይገኛል፡፡

በተለይም መስኖ ባለበት አካባቢ ምቹ ሁኔታዎች ስላሉ አርሶ አደሮች በአግባቡ ኩሬ አዘጋጅተው  በቀላሉ አሳን በማርባት ተጠቃሚ ከመሆናቸው ባሻገር ለሀገራዊ የዓሳ ምርትና ምርታማነት ዕድገት የድርሻቸውን ማበርከት ጀምረዋል፡፡

የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ ከተጀመረ ወዲህ የማምረት አቅምን በማሳደግ ግማሽ ሚሊዮን የነበረውን የዓሳ ጫጩት ምርትን  በ2018 ባጀት ዓመት ወደ 16.55 ሚሊዮን  ማድረስ ተችሏል፡፡ ይህ ደግሞ የዓሳ ጫጩቶቹን ለአርሶ አደሮቹ ተደራሽ ከማድረጉም ባለፈ የዓሳ ምርትና ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ እያሳደገ ይገኛል፡፡

በ2014 ዓ.ም እንደ ሀገር ከተፈጥሮ ውሃ አካላት 72.4 ሺህ ቶን፣ ከዓሣ ግብርና 0.74 ሺህ ቶን፣  በድምሩ 73.14 ሺህ ቶን የዓሳ  ምርት ነበር የተገኘው፡፡ በሌማት ቱሩፋቱ ኢኒሼቲቭ ምርቱ በእጅጉ እያደገ መጥቶ በ2018 በጀት ዓመት በጠቅላላ 276.7 ሺህ ቶን ዓሳ ለማምረት ታቅዶ 307.23 ሺህ ቶን ማምረት ተችሏል፡፡ ከዚህ ውስጥ ከዓሳ ግብርና የተገኘው 47.44 ሺህ ቶን ነበር፡፡

የአቅም ግንባታ ስራ፣  በዓሳ ግብርና የክላስተር አሰራርን መጠቀም እና ምርትና ምርታማነትን መጨመር የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን መተግበር ለውጤቱ መገኘት በምክንያትነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

የዓሳ ግብርናን ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡ ግብርና ሚኒስቴር በስፓኒሽ ኮኦፕሬሽን ፕሮጀክት በጀት ድጋፍ በኦሮሚያ ክልል  ጅማ ዞን ቀርሳ ወረዳ  በቶሊ ቀርሱ ቀበሌ በቴክኖሎጂ ተደግፎ የተሰራው የሙሉ ዓሳ ግብርና (የአኳካልቸር) ሰርቶ ማሳያን ለአሚኖና ቢያ የዓሳ እርባታ ማህበር ሰሞኑን ያስረከበውም ለዚህ ማሳያ ነው፡፡

{“remix_data”:[],”remix_entry_point”:”challenges”,”source_tags”:[],”origin”:”unknown”,”total_draw_time”:0,”total_draw_actions”:0,”layers_used”:0,”brushes_used”:0,”photos_added”:0,”total_editor_actions”:{},”tools_used”:{},”is_sticker”:false,”edited_since_last_sticker_save”:false,”containsFTESticker”:false}

እንደ ሀገር አንድ ዓይነት ፆታ ያላቸውን የቆሮሶ ዝሪያ ዓሳ ማስፈልፈያና ማባዣ ቴክኖሎጂ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ የተደረገውም በዚህ ቀበሌ ነው፡፡ በዚህ የሙሉ ዓሳ ግብርና ስራ ቦታ ላይ ያሉ 12 ኩሬዎችም በሳይንሱ መሰረት  የየራሳቸው ተግባር ያላቸው ሲሆኑ ከነዚህም የወላጆች ማቆያ፣ ማራቢያ፣ ማስፈልፈያ፣ ጫጩት ማሳደጊያና ማሰራጫ ኩሬዎችን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

የአሚኖና ቢያ የዓሳ እርባታ ማህበር አባላት 6 ሴቶችና 4 ወንዶች ሲሆኑ በደስታ የተረከቡትን የሙሉ ዓሳ ግብርና ስራን ውጤታማ አድርገው ራሳቸውን ከመለወጥ አልፈው በአካባቢው የዓሳ ክላስተር ለመፍጠር እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል፡፡ የዓሳ ምርቱን ለገበያ ለማቅረብም ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

የቀርሳ ወረዳ በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ የውሃ አማራጮች የታደለ በመሆኑ ለዓሳ ግብርና እጅግ ምቹ ነው፡፡ የወረዳው መስተዳድርም ይህንን ምቹ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት የተጀመረውን ስራ ለማስፋፋት፣ ገበያን ለማስተሳሰር እና ሰፊ የስራ ዕድል ለመፍጠር እንዲሁም የዓሳ እርባታ ክላስተር ለመፍጠር በዕቅድ እየሰራ ስለሆነ ያለው ተስፋ ብሩህ ነው፡፡  

ለ2019 በጀት ዓመት እንደሀገር 400 ሺህ ቶን ዓሳ ለማምረት ዕቅድ የተያዘ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ከዓሳ ግብርና ለማምረት የታቀደው 61.76 ሺህ ቶን ነው።

በአጠቃላይ በዓሳ ግብርና የታየው እምርታ አበረታች ቢሆንም እንደ ሀገር ካለው ምቹ ፀጋ ገና ብዙ ይቀራናል፡፡ በመሆኑም የዓሳ ግብርናን በፍጥነት በማስፋፋት ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው በቁርጠኝነት መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡