FDRE Ministry of Agriculture

የወጪ ንግድ ገቢን በማስገኘት እየጎመራ የመጣው የአቮካዶ ምርት

አቮካዶ በከፍተኛ የምግብ ነጥረ-ነገሮች የበለፀገ በመሆኑ እንዲሁም በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር ገበያ ያለው ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ ምክንያት በኢትዮጵያ ግብርና ውስጥ ትልቅ ትኩረት በማግኘት ከሆርቲካልቸር ንዑስ ዘርፍ አንዱ የልማት መስክ ሆኗል።
ኢትዮጵያ ቡናን ጨምሮ የተለያዩ ሰብሎችን በስፋት የምታመርት ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ለአቮካዶ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ በስፋትና በጥራት በማምረት አዲስ የወጪ ንግድ ገቢ ማስገኛ መንገድ ማድረግ ተችሏል፡፡ የአቮካዶ ምርት ዛሬ የውጭ ምንዛሪን በማስገኘት ፈጣን እድገት በማምጣት በስኬት እየገሰገሰ ይገኛል፡፡


የኢትዮጵያ ምቹ የአየር ጠባይ፣ ለም አፈር እና በቂ የዝናብ መጠን በተለይም በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በማዕከላዊ ኢትተጵያ፣ በሲዳማ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በኦሮሚያ እንዲሁም በአማራ ክልሎች ለአቮካዶ አመራረት ምቹ ሁኔታ አላቸው።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት አነስተኛ አርሶ አደሮችም ሆኑ በሰፋፊ እርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብቶች የአቮካዶ ምርትን ለማሳደግ በስፋት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።
በኢትዮጵያ በብዛት ከሚመረቱ የአቮካዶ ዝርያዎች መካከል የሃስ ዝርያ አንዱና ዋነኛው ሲሆን በተለይም የሃስ ዝርያ ለውጭ ሀገር ኤክስፖርት ገበያ ተፎካካሪ ነው፤ መንግሥት እና የልማት ድርጅቶችም የምርጥ ዘር ችግኞቹን ለአርሶ አደሮች በማቅረብና ስልጠናዎችን በመስጠት ዘመናዊ የምርት ስርዓትን ለማስፋፋት በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ።


ይህ ዓይነቱ ጥረት የምርትን፣ ጥራትን እና መጠንን በመጨመር የኢትዮጵያ አቮካዶ ወደ አውሮፓ እና መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በስፋት እንዲላክ መንገድ ከመክፈቱም ባሻገር ለአነስተኛ አርሶ አደሮች ከፍተኛ ገቢ በማስገኘትና ለወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
ተስማሚ የሆነ ቀዝቃዛ ማከማቻ እና የማጓጓዣ (Cold chain) አቅርቦት እጥረት፣ የገበያ ትስስር ውስንነት፣ የበሽታዎች መከሰት እና የዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎች እጥረት አሁንም የሚታዩ የዘርፉ ተግዳሮቶች ናቸው።
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የአቮካዶ ምርት ከፍተኛ የእድገት እቅም ያለው ሲሆን እነዚህን መሰረታዊ ተግዳሮቶች በመቅረፍ እና የድህረ-ምርት አያያዝን በማሻሻል ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ የአቮካዶ ገበያ ላይ አቅሟን አጠናክራ መውጣት ትችላለች።


የአቮካዶን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የተሻሻሉ የአቮካዶ ዝርያ ችግኞች በስፋት እየተባዙ ሲሆን በወጣቶች የተደራጁ በርካታ ኢንተርፕራይዞች የአቮካዶ እሴት ሰንሰለትን በመጨመር እያመረቱ ተጠቃሚነትንና የስራ እድልን በስፋት እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡
በኢትዮጵያም በተለይም ባለፉት 4 ዓመታት የአቮካዶን ምርት በስፋት ለማምረት ታቅዶ አመርቂ ውጤት ማግኘት የተቻለ ሲሆን ከዚህ ቀደም ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ብቻ ይውል የነበረውን የአቮካዶ ምርት ወደ ውጭ በመላክ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ማግኛ እየሆነ ነው።


በ2018 በጀት ዓመት በመደበኛ እና በክላስተር ከ157 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ላይ አቮካዶ በማልማት ከ28 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ማግኘት የተቻለ ሲሆን በ2019 በጀት ዓመት ደግሞ ከ182 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ከ37 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአቮካዶ ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ ነው፡፡
በቀጣይ 15 ዓመታትም ኢትዮጵያን የዓለማችን ቀዳሚ የአቮካዶ አምራችና ላኪ ሀገር ለማድረግ የሚያስችል ብሔራዊ የአቮካዶ ልማት ፕሮግራም ይፋ ተደርጎ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡