የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ በፈጠረው ምቹ ሁኔታ የወተት ምርት ጨምሯል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎችም ወተት አምራች አርሶአደሮች በማህበር በመደራጀት እሴት ጨምረው በመሸጥ የገበያ ማነቋቸውን ከመፍታት ባለፈ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ጀምረዋል፡፡
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ድጋፍ በማህበር ተደራጅተው ካላቸው የወተት ሀብት ፀጋ ተጠቃሚነታቸውን በማረጋገጥ የመልካም ተሞክሮ ባለቤት መሆን ከቻሉት ማህበራት መካከል ሀንዛት የወተት ውጤቶች መሽጫ መ/የህብረት ስራ ማህበር እና ቸምና የወተት ማቀነባበሪያ ህ/ሥራ ማህበር ግምባር ቀደም ናቸው፡፡

ሀንዛት የወተት ውጤቶች መሽጫ መ/የህብረት ስራ ማህበር በስልጤ ዞን ምስራቅ አዘርነት በርበሬ ወረዳ በቂልጦ 01 ቀበሌ የሚገኝ ሲሆን ሚያዚያ ወር 2017 ዓ.ም በ5 ሴቶችና 6 ወንዶች በድምሩ በ11 ወተት አምራች አርሶአደሮች ነበር የተቋቋመው፡፡ አሁን ላይ የአባላቱ ብዛት 25 ደርሷል፡፡
እያንዳንዱ አባላት የተሻሻለ የወተት ላም ዝሪያ ስላላቸው ማህበሩ ከአባላትና ከሌሎችም ወተት ሰብስቦ በማቀነባበር እሴት ጨምሮ ለተጠቃሚ ያቀርባል፡፡ የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም በገዛለት ማሽን በቀን እስከ 100 ኩባያ እርጎ በማሸግ ይሸጣል፡፡

ማህበሩ የስኬት ጎዳና ላይ ነው፡፡ ከአባላቱም ሆነ ከአካባቢው ወተት አምራች አርሶአደሮች በጥሩ ዋጋ ተረክቦ እሴት በመጨመር ደህንነቱና ጥራቱ የተጠበቀ ጤናማ ወተት ለተጠቃሚው ማህበረሰብ ተደራሽ ማድረግ ችሏል፡፡ በዙሪያ ወዳሉ ትልልቅ ከተሞችም የታሸገ እርጎ ያቀርባል፡፡
የማህበሩ ሰብሳቢ አቶ አደራ ረዲ እንደነገሩን ማህበሩ ስራ ከጀመረ በኋላ በ3 ወር ውስጥ የተሻሻለ ዝሪያ ያላቸውን 3 የወተት ላሞች ገዝቷል፡፡ አሁን ካፒታሉ 800 ሺህ ብር የደረሰ ሲሆን ማህበሩ በአካባቢው የነበረውን የገበያ ማነቆ በመፍታት አባላትንም ሆነ የአካባቢው ወተት አምራቾችን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል፡፡
ሌላው ማህበር በጉራጌ ዞን ጉመር ወረዳ በአረቅጥ ከተማ የወተት ላም ባላቸው 25 አርሶአደሮች የተመሰረተ ቸምና የወተት ማቀነባበሪያ ህ/ሥራ ማህበር ነው፡፡ ከተመሰረተ 2 ዓመት ሲሆን የአባላቱንም ብዛት 90 (61 ወንድና 29 ሴት) አድርሷል፡፡

ማህበሩ ከአባላቱም ሆነ ከሌሎች ወተት አምራች አርሶአደሮች 1 ሊትር ወተት በ70 ብር ተረክቦ በማሽን በማሸግ ጥራት ያለውን ጤናማ እርጎ ለተጠቃሞዎች ያቀርበል፡፡ ትዕዛዝ ካለ በቀን ብዙ መሸጥ ይችላል፡፡ ለምሳሌ የዘንድሮ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል በሆሳዕና ከተማ ሲከበር በቀን እስከ 500 ኩባያ የታሸገ እርጎ ያቀርብ ነበር፡፡

አሁን የማህበሩ ካፒታል 500 ሺህ ደርሷል ያሉት የማህበሩ ስራ አስኪያጅ አቶ መለሰ ወርቁ፤ አባላቱም ሆነ የአካባቢው ወተት አምራች አርሶአደሮች በጥሩ ዋጋ ሽጠው ተጠቃሚ መሆን፣ ጥራት ያላቸው ጤናማ የወተት ተዋፅዖዎችን (የታሸገ እርጎ፣ አይብና ቅቤ) ለተጠቀሚ ማህበረሰብ ማቅረብ እና ለ3 ሰዎች የስራ እድል መፍጠር ማህበሩ ያስገኛቸው ውጤቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ሁለቱም ማህበራት ወደፊት ስራውን በማስፋፋት እርጎ ብቻ ሳይሆን የታሸገ ወተትና ሌሎች የወተት ተዋፅዖዎችን ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ አቅድ አላቸው፡፡

ለሁለቱም ማህበራት ውጤታማነት የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም አስተዋፅዖ የላቀ ነው፡፡ ፕሮግራሙ የወተት ማቀነባበሪያ ማሽኖችን በመግዛት፣ ስልጠና በመስጠት፣ በክትትልና ሙያዊ ድጋፍ የማይተካ እገዛ አድርጎላቸዋል፡፡
አዘጋጅ፡- ሸምሱዲን ዩሱፍ
ፎቶግራፈር፡- ዮዲት እንዳለው
