FDRE Ministry of Agriculture

የወተት ላሞች አመጋገብ እና እንክብካቤ

ላሞችን በእርግዝና ወቅት በአግባቡ አለመመገብ በወተት ምርትና ምርታማነት፣ በላሚቷ የድህረ ወሊድ ጤና፣ በጥጃዋ ጤና እና አጠቃላይ እድገት ላይ አሉታዊ ተጽኖ ያሳድራል፡፡

ላሞችን በመጨረሻዎቹ 2 ወራት የተመጣጠነ መኖ መመገብ በወሊድ ጊዜ በጥሩ የሰውነት አቋም ላይ እንዲገኙ እና ጤናማ ጥጃ እንዲወልዱ ለማድረግ፣ የላሚቷን ወተት ማምረት አቅም ለማሳደግ፣ በወሊድና ድህረ ወሊድ ጊዜ ሊከሰቱ ከሚችሉ ችግሮች ለመከላከል ይረዳል፡፡

የወተት ላሞች የአመጋገብ ስርዓት

• ጥራታቸው እና የንጥረ ነገር ይዘታቸው ከፍተኛ ከሆኑ የተሻሻሉ የመኖ እጽዋት ዓይነቶች የተዘጋጀ ድርቆሽ፣ እርጥብ ሳር፣ ገፈራ፣ እንዲሁም በጥሩ ሁኔታ የተያዘ የተፈጥሮ ግጦሽ መኖ መመገብ፤

ሙሉዉን ፅሑፍ ለማንበብ ሊንኩን ይጫኑ

• መሰረታዊ መኖ እስኪጠግቡ፣ በቂ ማዕድን እና የመጠጥ ውሃ ያለገደብ 24 ሰዓት መስጠት፤

• በ8ኛው የእርግዝና ወር ላይ ላሞችን ጥራቱ ከፍተኛ የሆነ መሰረታዊ መኖ ያለገደብ መመገብ፤

• መሰረታዊ የመኖ ዓይነት ጥራት ዝቅተኛ ከሆን ተጨማሪ ከ 1-2 ኪ.ግ የድጎማ ምጥን መኖ መስጠት፤

• በ9ኛው የእርግዝና ወር ላሞችን ጥራቱ ከፍተኛ በሆነ መሰረታዊ መኖ ያለገደብ እና ተጨማሪ ከ1-2 ኪ.ግ ምጥን የወተት ከብት መኖ መመገብ፤

• መሰረታዊ የመኖ ዓይነት ጥራት ዝቅተኛ ከሆነ ተጨማሪ ከ3-4 ኪ.ግ የድጎማ ምጥን መኖ መስጠት ያስፈልጋል፡፡

በወሊድ ወቅት ለላሟ የሚደረግ እንክብካቤ፣ የሚታዩ ምልክቶችና የሚደረግላት እገዛ

• ላሟ ከመውለዷ ከ1 ሳምንት በፊት እና ከወለደች 1 ሳምንት በኋላ ከመንጋው የተለየ ንጹህና ደረቅ ቦታ ማዘጋጀት፤

• በመውለጃ ቦታዋ ላይ ድርቆሽ ወይም ገለባ መጎዝጎዝ፤

• መዉለጃዋ የተቃረበ ላምን ቢያንስ በቀን 2 ጊዜ መከታተል፤

• አንዲት ላም ለመዉለድ ከ1-2 ሳምንት  ሲቀራት ግቷ መለስለስ ወይም ማንፀባረቅ  ይጀምራል፤

• ለመውለድ 1 ቀን ሲቀራት የመቅበጥበጥ፣ ብቻዋን መሆንና  ከመንጋዉ የመለየት፣ ብልቷ የማበጥና ፈሳሽ መውጣት፣ ግቷና የጡቶቿ ማደግ አንዲሁም ወደ ታች መለጠጥ፤

• ለመውለድ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ የእንሽርት ዉሃ መፍሰስ፤

• የእንሽርት ውሃ መፍሰሱን እና የጥጃው አመጣጥ ትክክለኛ መሆኑን ማለትም ጥጃው በፊት እግሩና በጭንቅላቱ መምጣቱን ማረጋገጥ፤

• የጥጃው አቀማመጥ እና አመጣጥ ትክክለኛ ከሆነ እና ላሟ ማማጥ የምትችል ከሆነ ላሟ በራሷ እንዲትወልድ ጊዜ መስጠት፤

• በተሳሳተ መንገድ የመጣን ጥጃ ለማስተካከል ከመሞከር በፊት ላሟ መቆሟን ማረጋገጥ፤

•  ጥጃው እግር ላይ ገመድ በማሰር ገመዱን ላሟ ስታምጥ ብቻ መሳብና ማማጥ ስታቆም ማላላት፤

• የጥጃው ጭንቅላት እስከሚታይ ድረስ መሳብ እና ደረቱ ሲታይ ጥጃውን እንዳይታፈን ማዞር፤

• የእንሽርት ውሃ ከፈሰሰ ወይም የጥጃው ሸኮና ከታየ በኋላ ጥጃው በአንድ ሰዓት ዉስጥ ካልተወለደ እጅን አጽድቶ በማስገባት ማገዝ፤

• የጥጃው አመጣጥ ትክክለኛ ካልሆነ እና ችግር ከተፈጠረ የእንስሳት ጤና ባለሙያ እገዛ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡