በኢትዮጵያ የግብርና ታሪክ በተለይም በጥጥ ምርምር ረገድ ስሙ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል ነው።
በ1957 ዓ.ም በታችኛው አዋሽ ተፋሰስ የተከሰተው አደገኛ የጥጥ ተባይ የጥጥ ልማቱን በከፍተኛ ሁኔታ በመጉዳቱና ለጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች ጥጥ ማቅረብ ባለመቻሉ፣ ከውጭ ሀገር በግዥ ለመሸፈን እስከ 250 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ከፍተኛ ወጪ ተጠይቆ ነበር።

ይህንን ቀውስ በዘላቂነት ለመፍታት በምርምር የተደገፈ መፍትሔ ለማምጣትና የሀገር ውስጥ ምርታማነትን ለማረጋገጥ ሲባል በ1 ሺህ 350 ሄክታር መሬት ላይ የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል በ1957 ዓ.ም ተመሰረተ።
ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ማዕከሉ የሀገሪቱን የጥጥ ዘርፍ በማሳደግ ረገድ የማይተካ ሚና ሲጫወት ቆይቷል። በአሁኑ ወቅት ማዕከሉ በ8 የተለያዩ ቁልፍ የምርምር ዘርፎች ላይ ተሰማርቶ ለሀገሪቱ የበኩሉን በማበርከት ላይ ይገኛል።

የተሻለ ምርት የሚሰጡና ተባዮችን መቋቋም የሚችሉ 45 የጥጥ ዝርያዎችን በማፍለቅ ለጥጥ አብቃይ አካባቢዎች አሰራጭቷል። ከዚህም በላይ ማዕከሉ 700 የጥጥ ዘረመሎችን በመያዝ ለቀጣይ ትውልድና ምርምር ታላቅ የቴክኖሎጂ ባንክ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል በቤተ-ሙከራና በምርምር ጣቢያዎች ብቻ ሳይወሰን፣ የምርምር ውጤቶችን ወደ አርሶና አርብቶ አደሩ ዘንድ ለማድረስ ሰፊ የቴክኖሎጂ ሽግግር ስራዎችን ሰርቷል። በዚህም የተሻሻሉ የጥጥ ዘሮችን በአርሶና አርብቶ አደር ማሳ ላይ በማባዛትና በማስተዋወቅ ስኬቶችን አስመዝግቧል።

አዳዲስ የዘር ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ ለኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪና ለግብርናው ዘርፍ እንዲሁም ለሀገር ኢኮኖሚ እያበረከተ ያለው ድርሻ ከፍተኛ ነው፡፡
እንዲሁም ማዕከሉ የስንዴ፣ ሰሊጥ፣ ቴምር እና የሌሎች ሰብሎች ዝርያዎችን በማፍለቅ ውጤቶችን ያስመዘገበ ሲሆን በተለይ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ሂደት የመስኖ ስንዴን በማስጀመር ለውጤት በማብቃት ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡

ለወረር ግብርና ምርምር ማዕከል ትልቅ የመስኖና የተፈጥሮ ጸጋ ሆኖ የሚያገለግለው ታላቁ የአዋሽ ወንዝ በሌላ በኩል የጎርፍ አደጋ ስጋት ደቅኖበታል።
በመሆኑም ማዕከሉ ከጎርፍ አደጋ እንዲታደግ ከሚመለከታቸው አካላት ሁሉ አስቸኳይ ትኩረትና ዘላቂ መፍትሔ ይሻል።
