ወልደያ ድልድይ በሐረሪ ክልል ኤሬር ወረዳ ወልደያ ቀበሌ ውስጥ ከሩቅ ኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች የሚመጡ ሁለት ትልልቅ ወንዞች የሚገናኙበት ቦታ ላይ የተገነባ ድልድይ ነው፡፡ ወንዞቹ ፈላና እና ገፍራ ይባላሉ፡፡ ገፍራ ወንዝ ከጃርሶ ወረዳ ከፍታ አካባቢ የሚመጣ ሲሆን ፈላና ወንዝ ከኮምቦልቻ ወረዳ ነው የሚመጣው፡፡

ቦታው ከአምስት አቅጣጫዎች (ከባቢሌ፣ ጉርሱም፣ ጃርሶ፣ ኮምቦልቻ እና ከሐረር) የሚመጡ መንገደኞች የሚገናኙበትና የሚተላለፉበት ስለሆነ በሁለቱ ወንዞች ጎርፍ የከፋ አደጋ ይደርስ ነበር፡፡
ነዋሪዎቹ እንደገለፁት የክረምት ወቅት ለአካባቢው ነዋሪዎች መከራ ነበር፡፡ ወንዞቹ በጎርፍ ሲሞሉ የቤተሰብ አባላት ማዶ ለማዶ ከመተያየት ውጪ መገናኘት አይችሉም፤ የሚያጠቡ እናቶች ከልጆቻቸው ተለያይተው ያድሩ ነበር፡፡
ጎርፉ ሞለቶ ሲመጣ ከፍተኛ ጉዳት ያደርስ ነበር፡፡ ያገኛውን ሰውና እንስሳት ጠራርጎ ነበር የሚሄደው፡፡ በየጊዜው የሰው ህይወት ይቀጥፍ ነበር፡፡ በቀበሌው ፀሐይ እያለ ኮመቦልቻ ወይም ጃርሶ አካባቢ ሲዘንብ ድንገት የሚመጣው ደራሽ ጎርፍ ንብረትን ከማውደም በላይ የሰውን ህይት ይቀጥፍ ነበር፡፡

ድልድዩ ሲሰራ እናት ጤና ጣቢያ ወልዳ በአንቡላንስ ወደ ቤቷ ሲትመልስ በደራሽ ውሃ ተይዛ በህዝቡ ርብርብና በማሽን እገዛ መትረፏን የቅርብ ጊዜ ትዝታውን ያወጋን በኤሬር ወረዳ የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፐሮግራም ድጋፍ ሰጪ አቶ ባህር ዩሱፍ ነው፡፡
እንዲሁም በአካባቢው በክረምት ወቅት በስፋት የሚመረቱ ማንጎ፣ ሸንኮራና ሎሚ ምርቶችን ወደ ገበያ ማቅረብ አስቸጋሪ ነበር፡፡ መንጎ ተሰብስቦ አንድ ሳምንት ስለሚቆይ በስብሶ የሚቀርበት ሁኔታ ነበር፡፡ በአብዛኛው ምርቶቹ ይበላሹ ነበር፡፡
በግብርና ዕድገት ፕሮግራም II ተጀምሮ በክልሉ ግብርና ቢሮ እና በምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ትብብር ተገንብቶ በቅርቡ በመመረቅ አገልግሎት እየሰጠ ያለው ወልደያ ድልድይ የተጠቀሱ ችግሮችን ከመሰረቱ ፈቷል፡፡

ድልድዩ ከተሰራ ወዲህ ነዋሪዎቹ አመቱን ሙሉ በሰላም ወጥተው የልማት ስራዎችን ሰርተው በሰላም ይገባሉ፤ ምርታቸውን ያለምንም እንቅፋት ወደ ገበያ መውሰድ ችለዋል፡፡ በክረምት ወቅት ከአምስቱም አቅጣጫዎች የሚመጡ መንገደኞችም ያለምንም እንቅፋት በሰላም ያልፋሉ፡፡
በአካባቢው እየጨመረ የመጣው የግብርና ምርትና ምርታማነት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት የሚያፋጥን ሲሆን ለዚህም ውጤት የወልደያ ድልድይ ጉልህ ሚና አለው፡፡
በአጠቃላይ የማህበረሰቡን ችግር ከመሰረቱ በመፍታት በዘላቂነት ልማትን የሚያግዝ ስራ ላይ የሚውለው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡
ዘጋቢ፡- ሸምሱዲን ዩሱፍ
ፎቶግራፈር፡- ዮዲት እንዳለው