
እንጉዳይ በክሎሮፊል አልባ ፈንገስነት የሚመደብ፣ የግብርና ተረፈ-ምርቶችን ወደ ምግብነት የሚቀይር እንዲሁም ለጤና ከሚሰጠው ጠቀሚታው ባለፈ ከፍተኛ ኢኮኖሚያው ፋይዳ ያለው ነው፡፡
እንጉዳይ በፕሮቲን፣ በቫይታሚን ቢ እና ዲ፣ በካልሲየም፣ በፖታሲየም እና በሴሊኒየም የበለጸገ በመሆኑ ለምግብነት ሲውል ለጤናማ ትውልድ ግንባታ የሚያበረክተው አስተዋፅዖው የላቀ ነው።
ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን በተመለከተ በአነስተኛ ቦታ ላይ ስለሚመረት ለከተማ ግብርና ምቹ በመሆኑ ለአልሚው በቀላሉ ገቢ ያመነጫል፤ የሥራ ዕድልም ይፈጥራል።
የእንጉዳይ አይነቶች በተን፣ ሺታኪ እና ኦይስተር የሚባሉ ሲሆኑ ትኩረት የሚናደርገው በኦይስተር የእንጉዳይ ዓይነት ላይ ነው፡፡ ለማይሲሊያው (ለእንጉዳይ ህብረ-ሥር) እድገት የሚያስፈልገው ሙቀት 20 እስከ 25oC ሲሆን አስፈላጊው የአየር እርጥበት ከ85 እስከ 95 በመቶ ነው፡፡
እድገቱ የሚወስደው ጊዜ ከ25 እስከ 30 ቀናት ሲሆን ምርታማነቱን በተመለከተ ከ1 ኪ.ግ ሰብስትሬት (የእንጉዳይ ማሳደግያው) እስከ 800 እስከ 900 ግራም ምርት ይገኛል።
የኦይስተር እንጉዳይ አመራረት ሂደት
ቦታ እና ቤት ግንባታ፦ ንጹህና ከብክለት የራቀ ቦታ ያስፈልጋል። ማምረቻው 3 ክፍሎች (የምርት ክፍል፣ የጨለማ ክፍል እና የዘር መዝሪያ ክፍል) ይኖሩታል።
መደርደሪያ አደረጃጀት፦ ከእንጨት/ብረት የሚሰራ ሆኖ ቁመቱ 1.8 ሜትር፣ ስፋቱ 0.6 ሜትር እና 4 ደረጃዎች ያሉት መሆን አለበት።
የሰብስትሬት ዝግጅት፦ ዋና ግብዓቶቹ የጥጥ ፍሬ፣ ገለባ (ስንዴ/ጤፍ/ገብስ) እና ሰጋቱራ ናቸው። ተጨማሪ ግብዓቶች የስንዴ/ሩዝ ፍሩሽካ እና ጅፕሰም ሲሆኑ ቀመርን በተመለከተ 89 በመቶ ጥጥ ፍሬ/ገለባ + 10 በመቶ ፍሩሽካ + 1 በመቶ ጅፕሰም ሲሆን እርጥበቱ ከ60 እስከ 70 በመቶ መሆን አለበት።
ማከም፦ ጀርሞችን ለማጥፋት በፈላ ውሃ/እንፋሎት (በ121°C ለ3 ሰዓታት) ማምከን (በሽታ አምጪ ተዋህሲያንን ከግብዓቶቹ ማስወገድ)።
ዘር መዝራት፦ ከ3 እስከ 4 በመቶ መጠን ያለው የእንጉዳይ ዘር ከቀዘቀዘው ሰብስትሬት ጋር ይቀላቀላል።
የእድገት ደረጃዎች፦ የማይሲሊያ (የእንጉዳይ ህብረ-ሥር) እድገት ለ21 ቀናት በጨለማ ክፍል ውስጥ ይቆያል፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ ሙቀት ከ20 እስከ 25oc፣ እርጥበት 65 እስከ 70 በመቶ ይሆናል። እድገቱን በተመለከተ የእንጉዳይ ማሳደግያው በእንጉዳይ ህብረ-ሥር ከተሸፈነ በኋላ ወደ ብርሃን ክፍል ይዛወራል። በቀን 3 ጊዜ ውሃ ይረጫል፤ በቂ አየርና ብርሃን እንዲያገኝ ይደረጋል።
በሽታዎች/ተባዮች እና መከላከያ ዘዴዎች
አረንጓዴ ሻጋታ፦ በ4 በመቶ ፎርማሊን (ማፅጃና ፀረ-ህዋስ) ማከም ወይም የተበከለውን የእንጉዳይ ማሳደግያ ማስወገድ/ማቃጠል።
የቀለም ኮፍያ፦ ከከፍተኛ እርጥበት የሚከሰት የፈንገስ አረም ነው፡፡ ደረቅ ገለባና ጥራት ያለው የእንጉዳይ ማሳደግያ በመጠቀም መከላከል ይቻላል።
ብራውኒንግ፦ በባክቴሪያ የሚመጣ በሽታ ነው፡፡ በእንጉዳዩ ላይ ቀጥታ ውሃ አለመርጨት።
ተባዮች (ዝንቦችና አይጦች)፦ የመስኮት ወንፊቶችን መጠቀም፣ የዝንብ ወጥመድ ማድረግ፣ የፓኬጅ ፕላስቲኮችን ከአይጥ መጠበቅ፡፡
ምርት መሰብሰብ፣ ድህረ-ምርት እና ገበያ
ምርት መሰብሰብ፦ ውሃ መጠጣት ከጀመረ ከ7 እስከ 10ኛው ቀን የመጀመሪያው ምርት ይሰበሰባል። ለገበያ እስከ 3ኛ ዙር ማምረት ይቻላል። ከማጨድ 1 ቀን በፊት ውሃ ማቆም ያስፈልጋል።
ማቆየት፦ ምርቱ በፍጥነት ስለሚበላሽ በማቀዝቀዝ ወይም በማድረቅ ማቆየት ይቻላል።
ገበያ፦ ከሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች እና ከሱፐር-ማርኬቶች ጋር ትስስር መፍጠር ነው።
እንጉዳይን የሚያመርት ሰው ለተጨማሪ መረጃ ባለሙያን ማማከር ያስፈልጋል፡፡
