ሀዋሳ፣ ግንቦት 20/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) የእንስሳት ጤና እና ደህንነት አዋጅ 1376/2017 ላይ ከሲዳማ፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ እና ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ለተውጣጡ የዘርፉ አመራሮች እና ለአዋጁ አስፈጻሚ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሂዷል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሳ ሃብት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ወ/ሮ ፅጌሬዳ ፍቃዱ የእንስሳትን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በእንስሳት ጤና አጠባበቅ፣ ዝርያ ማሻሻል እና መኖ ዝግጅት ላይ መንግስት አበክሮ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የእንስሳትን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በሚደረገው ርብርብ የእንስሳት ጤና እና ደህንነት አዋጅ ሚናው የላቀ ነው ያሉት አማካሪዋ፣ ለአዋጁ ተግባራዊነት ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

በሲዳማ ክልል የእንስሳት ሃብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶ/ር ሚሊዮን ዮቴ በበኩላቸው እንስሳት መሰረታዊ ፍላጎት እንዲሟላላቸው የሚሹ ፍጡራን መሆናቸውን ጠቁመው በእንስሳት አያያዝ ላይ ያሉ ክፍተቶችን በዘላቂነት ለመፍታት አዋጁ አይነተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡

ለግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ዝግጅት በአውሮፓ ህብረት የሚደገፈው ሪስቶር ፕሮጀክት የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፡፡
የፌደራልና የክልል የስራ ኃላፊዎች በመድረኩ የተገኙ ሲሆን ተሳታፊዎቹ የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የእንስሳት ህክምና ቤተ-ሙከራዎችን እንዲሁም የእንስሳት ደህንነትና ጤና ማዕከልን ጎብኝተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ዮሐንስ ደመቀ
ፎቶ፡ ማቲዎስ ተገኝ
