(አዳማ፣ ሕዳር 26 ቀን 2018 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር)
በእንስሳት ዘርፍ ምርታማነትን ለማሳደግ እና የሕዝብ ጤና ደኅንነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ በሆነው በእንስሳት ጤና ጥበቃ ዙሪያ፣ በተለይም የእንስሳት በሽታዎችን ቀድሞ ለመለየት፣ እንዳይከሰቱ ለመከላከልና ቢከሰቱም በፍጥነት ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የአቅም ግንባታ ላይ ትኩረት ያደረገ ሰፊ ስራ እየተከናወነ ይገኛል። ይህ ሥራ የእንስሳት ዘርፉ ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ሽግግር፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለውጭ ንግድ ገቢ ያለውን ከፍተኛ ድርሻ ለማጠናከር ያለመ ነው።

የእንስሳት ጤና ባለሙያዎች ድንበር ዘለል በሽታዎች ስጋት ለመቀነስ እና ወረርሽኞችን ቀድሞ በመለየት፣ ለመከላከል እና ቢከሰቱም በፍጥነት ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የአቅም ግንባታ ስልጠና ለአምስት ተከታታይ ቀናት ወስደዋል። ስልጠናው በንድፈ ሃሳብና በተግባር የተደገፈ ሲሆን፣ ሰፊ ውይይት እና የልምድ ልውውጥ የተካሄደበት ነው።

በቅድመ-መከላከል ላይ የተመሰረተውን ይህን ስራ ለማጠናከር፣ ከዓለም የምግብና የግብርና ድርጅት (FAO) የድንገተኛ አደጋ ማኔጅመንት ማዕከል (EMC) ጋር በመተባበር ለእንስሳት ጤና ድንገተኛ አደጋዎች ኦፕሬሽኖች አስተዳደር ብሔራዊ ማኑዋል ተዘጋጅቷል። ይህ ሰነድ በበሽታ ወረርሽኝ ጊዜ በሪፖርት አቀራረብና በምርመራ ላይ የታዩ ድክመቶችን ለመቅረፍ እና የድንገተኛ አደጋ ዝግጅትና ምላሽ አሠራርን ለማሻሻል ያለመ ነው።

ማኑዋሉ የወረርሽኝ ዞኖችን የመለየት፣ የእንስሳት ለይቶ ማቆያ አሠራሮችን እና የእንቅስቃሴ ቁጥጥርን ጨምሮ የእንስሳት ወረርሽኝን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ መርሆችን ያስቀምጣል። የአምስት ቀኑ ስልጠናም በረቂቁ ማኑዋል ላይ የቀረቡትን ተግባራት ለመፈተሽ የማስመሰል ልምምድ (SIMEX) አካቷል። አገልግሎቱ በዋናነት የሚያተኩረው በአደጋው ቅድመ ማስጠንቀቂያ ምዕራፍ ላይ ሲሆን፣ ይህም የአደጋ ምልክት ሲታይ ወይም በአጎራባች አገሮች የተረጋገጠ ወረርሽኝ ስጋት ሲደቅን የቅድመ መከላከል ተግባራትን መተግበርን ያካትታል።

በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ ሰልጣኞቹ በቂ እውቀትና ክህሎት ማግኘታቸውን በመግለጽ፣ ይህን አቅም ወደ ታች በማውረድ ለሌሎች ባለሙያዎች በማጋራት እንዲሁም አርሶና አርብቶ አደሩ ስለበሽታው ምንነት ግንዛቤ እንዲጨብጥ በማድረግ የአርሶ አደሩን ተደራሽነት ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።

ዘጋቢ፡- ጌዲዮን ነጋሸ
ካሜራ፡- ዮዲት እንዳለው
