ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የእንስሳት ፀጋ በመጠቀም የዘርፉን ምርታማነት በአይነት፣ በመጠንና በጥራት ለማሳደግ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ ተጨባጭ የምርታማነት እድገት ተመዝግቧል፡፡
የእንስሳት ሀብቱ ለአርብቶ እና ለአርሶ አደሩ የኑሮ መሰረት፣ ለምግብና ስነ-ምግብ ዋስትና መረጋገጥ እንዲሁም ለአገራችን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ትልቅ ሚና አለው፡፡
በተለይ የወጭ ንግዱን በመደገፍ ሂደት የራሱን ድርሻ እየተወጣ ሲሆን የቁም እንስሳት እና የእንስሳት ተዋፅኦ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ ቡናን በመደገፍ የግብርናው ዘርፍ ለውጭ ምንዛሪ የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ እያሳደገ ይገኛል፡፡
የእንስሳት ሃብት ልማት በወጭ ንግድ ያለውን አበርክቶ በተሻለ ደረጃ ማሳደግ እንዲቻል የእንስሳት መረጃ አያያዝ ሥርዓትን ማጠናከር ይገባል፡፡
በኢትዮጵያ የእንስሳት ዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ፣ የእንስሳት በሽታን ለመከላከልና አገራችን የእንስሳት ገበያ መዳረሻዎችን እንድታሰፋ ለማስቻል የግብርና ሚኒስቴር ባለፉት ሁለት አመታት ዘመናዊ የእንስሳት መረጃ አያያዝ ስርዓትን በመዘርጋት የእንስሳት ልየታ፣ ምዝገባና ክትትል ስርዓትን በአርብቶ አደሩ አካባቢ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል፡፡ እነዚህን የእንስሳት መረጃዎችን ለመመዝገብ፣ ለመቆጣጠርና ለመከታተል የሚያስችል የዳታ ሰርቨር ማዕከል በሚኒስቴር መ/ቤቱ ተገንብቷል፡፡
የእንስሳት ልየታ፣ ምዝገባና ክትትል ስርዓት ተግባራዊ መደረጉ ለአርብቶና አርሶ አደሩ እንዲሁም ለሀገር ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን የሚያበረክት ሲሆን በዋናነትም የእንስሳት አያያዝን ለማዘመን፣ የእንስሳት ተዋፅኦ ደህንነትና ምርት ክትትልን ለማጠናከር፣ የእንስሳት ዝርያና ምርታማነትን ለማሻሻል፣ የበሽታ ቁጥጥርን ለማጠናከር፣ የገበያ ተወዳዳሪነትን እና የእንስሳት ኢንሹራንስ ተደራሽነትን ለማሳደግ ትልቅ ድርሻ አለው፡፡
ይህ ዘመናዊ አሰራር እንስሳው ከውልደት ጀምሮ ያለበትን ቦታ፣ እንስሳው የወሰደውን የክትባት አይነት፣ ዝርያና ሌሎች ተያያዥ መረጃዎች የሚመዘገብበት ዘመናዊ አሰራር ነው፡፡
በተለያዩ የአርብቶ አደር አካባቢዎች ተግባራዊ የተደረገው የእንስሳት ልየታ፣ ምዝገባና ክትትል ስርዓት በበጎች፣ ፍየሎች፣ የቀንድ ከብቶችና ግመሎች ላይ የጆሮ ላይ መለያ (Ear Tagging) በማድረግ እየተሰራበት ሲሆን አርብቶ አደሩ ካለው ሰፊ የእንስሳት ሃብት እንዲጠቀም ያነሳቸው የነበሩ የገበያና ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን እየፈታ ይገኛል፡፡
አርብቶ አደሮች ዘመናዊ የእንስሳ መረጃ ስርዓቱን ጠቀሜታ በመረዳት ከዚህ በፊት ይጠቀሙበት የነበረውን አካላዊ መለያ በጆሮ ላይ መለያ እየተኩት ይገኛሉ፡፡
