FDRE Ministry of Agriculture

የእንስሳት እና ዓሳ ሀብት ሽግግር በመደመር መንግስት!

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) የግብርና ሚኒስቴር እና የተጠሪ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ሞዴል ፈፃሚዎች ሰራተኞች በተገኙበት “የእንስሳት እና ዓሳ ሀብት ሽግግር በመደመር መንግስት!” በሚል መሪ ሃሳብ በዛሬው ዕለት ውይይት ተደርጓል።

በእንስሣት ሀብት ልማት ዘርፍ ላይ በመደመር መንግስት የተጀመረው “የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ” በዋናነት የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ላይ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር አዲሱ አረጋ ተናግረዋል።

በዚህም በእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ስራ ላይ በምሳሌነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ተስፋ ሰጪ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ሚኒስትሩ አያይዘውም በዶሮ እርባታ፣ በወተት ልማት፣ በእንስሳት ጤና እንዲሁም በሌሎች የእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፍ ላይ በተመሳሳይ በተከናወኑ ስራዎች ተስፋ ሰጪ ስኬቶች እየተመዘገቡ መሆኑን ገልጸዋል።

የመኖ ልማቱ እንዲዘምን የመኖ ማቀነባበሪያዎችን በተለያዩ የሃገራችን አካባቢዎች የማስፋፋት ስራም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

አጠቃላይ የእንስሳት ሀብት ልማት ኤክስቴንሽን ስርዓቱን አሁን ካለበት ደረጃ የበለጠ እንዲጠናከር በማድረግ የዘርፉን ምርታማነት ማሳደግ ሌላኛው ትኩረት ተሰጥቶት መሰራት ያለበት ጉዳይ መሆኑንም ሚኒስትሩ አንስተዋል።

“የእንስሳት እና ዓሳ ሀብት ሽግግር በመደመር መንግስት!” በሚል ርዕስ ለውይይቱ የመነሻ ፅሁፍ ያቀረቡት በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት እና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

የመደመር መንግስት የእንስሳት ሀብት ልማት ሽግግር ዓላማ ዘመናዊ፣ ዘላቂ፣ አካታችና የማይበገር የእንስሳት ሀብት ልማትን ማሳለጥ መሆኑንም ዶ/ር ፍቅሩ ባቀረቡት ጽሁፍ አንስተዋል።

በግብርናው ዘርፍ በርካታ የሪፎርም ስራዎች እየተከናወኑ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ አንዱ “በመደመር መንግስት እይታ የግብርና እመርታ!” በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ቀጣይነት ያላቸው ስልጠናዎች ለዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች እየተሰጡ ይገኛል፡፡

ዘጋቢ፦ ሰለሞን ደምሰው

ፎቶ፦ ተክለመድህን አቻምየለህ