/አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19 ቀን 2018 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር/
በግብርናው ዘርፍ በእንሰሳት ሀብት ልማት እየተመዘገበ ላለው ምርታማነት ዕድገት የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ኤክስቴንሽን አገልግሎት ድርሻውን እየተወጣ ይገኛል፡፡
የኤክስቴንሽን አገልግሎት ተደራሽነት ማስፋት እና የቴክኖሎጂና ዘመናዊ የአሰራር ዘዴ ሽፋንን ማሳደግ የዘርፉን ምርታማነት ይጨምራል፡፡

ግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት ዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግና የሚጠበቀውን ምርት ለማሳካት እራሱን የቻለ የእንስሳት ልማት ኤክስቴንሽን አገልግሎት አሰጣጥ እስከ አርሶና አርብቶ አደሩ ድረስ በማውረድ እየሰራ ይገኛል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና አሳ ሃብት ልማት ኤክስቴንሽን መሪ ሥራ አስፈጻሚ መላክ አሰፋ የዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንና በዋናነትም የእንስሳትና አሳ ሃብት ልማት ኤክስቴንሽን ፓኬጅ በማዘጋጀት እስከ አርሶና አርብቶአደሩ ድረስ እንዲደርስ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
የኤክስቴንሽን ስትራቴጂው ሁሉንም የእንስሳት ልማት እሴቶች በማካተት የከተማ ግብርና፣ የጥምር ግብርና፣ የአርብቶና ከፊል አርብቶአደርን ተደራሽ በሚያደርግ መልኩ የተዘጋጀ ነው፡፡
የኤክስቴንሽን አገልግሎት መስፋፋት መገለጫው አርሶና አርብቶ አደሩ የተሻለ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ሲቻል እንደሆነ አቶ መላክ ገልፀዋል፡፡
ለዚህም በተሰራው ሰፊ ስራ የእንስሳት ኤክስቴንሽን ተጠቃሚዎችን ከ12 ሚሊዮን በላይ፣ የፓኬጅ ተጠቃሚዎችን ከ6 ሚሊዮን በላይ እንዲሁም ከ300 ሺህ በላይ ሞዴል አርቢዎችን መፍጠር ተችሏል፡፡
ሞዴል አርቢዎች የእንስሳት ኤክስቴንሽን ፓኬጆችን በመጠቀም በወተት፣ በማር፣ በስጋ፣ በእንቁላልና ዶሮ እንዲሁም በአሳ ልማት ምርታማነታቸውን ያሳደጉ ሲሆኑ ቴክኖሎጂን ከማስፋፋት አንጻር ልምዳቸውንና ተሞክሯቸውን ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዲያስፋፉ እተደረገ ነው፡፡
ዘጋቢ፡- ተዋበ ጫኔ
ፎቶግራፈር፡- ማቲዎስ ተገኝ