ሸገር፣ ጳጉሜን 5/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) ግብርና ሚኒስቴር የኢትዮጵያ እንስሳት መለያ እና ክትትል ስርዓት የወተት ላሞችና ጥጆች ላይ ተግባራዊ የማድረግ ዘመቻ በሸገር ከተማ አስጀምሯል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት ጤና እና ቬተርነሪ ፐብሊክ ሄልዝ መሪ ስራ አስፈጻሚ ሲሳይ ጌታቸው (ዶ/ር) የእንስሳትን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የዘመነ የመረጃ ስርዓት አስፈላጊነትን ገልፀው በሚኒስቴር መ/ቤቱ ዘመናዊ የእንስሳት የመረጃ ስርዓት ተገንብቶ ወደ ተግባር እንደተገባ ተናግረዋል፡፡
የመረጃ ስርዓቱ የእንስሳትን አጠቃላይ መረጃ መመዝገብ፣ መለየት እና መከታተል የሚያስችል እንደሆነ ያነሱት መሪ ስራ አስፈፃሚው በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ የእንስሳት ወደ አንድ ማዕከላዊ የመረጃ ቋት የሚያመጣ ስርዓት ነው ብለዋል፡፡
ስርዓቱ የእንስሳቱ ምርት በአለም ገበያ ተወዳዳሪነታቸው እንዲጨምር፣ ጥሩ ምርት የሰጡ እንስሳት ዝርያዎችን ለማስቀጠልና ለማሻሻል እንዲሁም ለበሽታ ቁጥጥር፣ ክትትልና መከላከል አይነተኛ ሚና እንደሚጫወት አስገንዝበዋል፡፡
ዶ/ር ሲሳይ አክለውም ስርዓቱ አርቢዎች ከፋይናንስ ተቋማት ብድር ለማግኘት እንስሳቶቻቸውን እንደ መያዣ በመጠቀም በቀላሉ መበደር እንደሚችሉ ገልፀዋል፡፡
በሸገር ከተማ አስተዳደር የኮዬ ፈጬ ክፍለ ከተማ ምክትል አስተዳደር አቶ ኬንቦን ሞቱማ በበኩላቸው የመረጃ ስርዓቱ ለእንስሳት አርቢዎች ያለውን ፋይዳ በመግለፅ ስርዓቱ በማስተዋወቅ ግብርና ሚኒስቴር ላበረከተው አስተዋፅዖ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የኔዘርላንድ የልማት ድርጅት የወተት ላሞች የመረጃ አያያዝ የአቅም ግንባታ ስልጠና እና የወተት ላሞች መታወቂያ ቁጥር የያዘ (Ear Tag) አበርክቷል፡፡
የዘመቻ ስራው በቀጣይ በኦሮሚያ ክልል አርሲ፣ ምዕራብ አርሲ እና ሰሜን ሸዋ ዞኖች፣ እንዲሁም በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን በተመረጡ የወተት ተፋሰስ አካባቢዎች ይካሄዳል፡፡
