የእንስሳትና አሳ ሀብት ሴክተር ልማት ፕሮጀክት በዋና ዋና የግብርና እሴት ሰንሰለቶች ምርታማነት እና የገበያ ተወዳዳሪነትን በማሳደግ ላይ ያተኮረ ነው፡፡
ፕሮጀክቱ ከዓለም ባንክ በተገኘ 176 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ብድር የሚደገፍ ሲሆን በስድስት አመት ጊዜ እና ለ2 ዓመታት ተጨማሪ ማራዘሚያ እ.ኤ.አ ከ2018-2026 እየተተገበረ ያለ ነው።

የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ በተመረጡ የእንስሳት እሴት ሰንሰለቶች (በወተት፣ ቀይ ስጋ፣ እንቁላልና ዶሮ እና የዓሳ እርባታ) የአምራቹን እና አቀነባባሪዎችን ምርታማነት እና ኮሜርሻላይዜሽን ማሳደግ፣ የእንስሳትና ዓሳ ዘርፍ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓትን ማጠናከር እንዲሁም ለድንገተኛ አደጋ ፈጣንና ውጤታማ ምላሽ መስጠት ነው።

የእንስሳትና ዓሳ ሴክተር ልማት ፕሮጀክት የአርሶአደሩን የገበያ ትስስር፣ ተቋማዊና ፕሮግራሞች ማጠናከር፣ የፕሮጀክት ማስተባበር እና የእውቀት አጠቃቀም ማሻሻል ላይ ባሉ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ በማተኮር ለእንስሳት ምርታማነት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።
በአሁኑ ወቅት በ9 ክልሎች፣ በ58 ወረዳዎች እና በ1,755 ቀበሌዎች 2.2 ሚሊዮን ቀጥተኛ ተጠቃሚዎችን በመያዝ በአነስተኛ አርሶአደሮች፣ በወጣቶችና ሴቶች ቡድኖች፣ በህብረት ስራ ማህበራት እንዲሁም በዩኒየኖች ላይ እየተተገበረ ይገኛል።
ከምርታማነት ባለፈ የእሴት ሰንሰለቶቹን ምርት ማቀነባበርና እሴት ጭመራዎችን ከግብይት ጉዳዮችጋር ያስተሳስራል፡፡

የተሻሻሉ ዝርያ አቅርቦትና ስርጭት፣ የአሳ ጫጩት ብዜት፣ የመኖ ልማት፣ የእንስሳት ጤና እና ኤክስቴንሽን አገልግሎት፣ የአቅም ግንባታ እና የመሰረተ-ልማት ዝርጋታ፣ የምርት ማከማቻና የገበያ ማዕከላትን ፕሮጀክቱ አደራጅቷል፡፡ በዚህ ሂደት የመንግስት ተቋማት፣ አርሶአደሮች፣ የህብረት ስራ ማህበራት እና ዩኒየኖች ተሳታፊ ናቸው፡፡
እነዚህ ተግባራትን ማከናወን የተሻሻሉ የእንስሳትና የዓሳ እርባታ ምርትና ግብይት መፍጠር፣ የእንስሳት ምግብ ተዋፅኦን ማሳደግ፣ በእንስሳት ሃብት ዘርፍ የሥርዓተ-ፆታ እና የወጣቶችን ተጠቃሚነት ማሳደግ፣ የአነስተኛ አርሶአደሮችን ኑሮ ማሻሻል፣ የእንስሳት ህክምና አገልግሎትን ማስፋት እና የህብረት ስራ ማህበራትን ማጠናከር ከፕሮጀክቱ የሚጠበቁ ውጤች ናቸው፡፡
በዚህም የአርሶአደሮችን ገቢ በማሳደግ፣ ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር እና የምግብ እና የስነ ምግብ ዋስትናን በማሻሻል ላይ ይገኛል። በቀጣይ የእንስሳትና የአሳ ሀብት ልማትን ወደ ዘላቂና ኮሜርሺያላይዜሽን ዘርፍ ለማሸጋገር የራሱን ሚና መጫወቱን ቀጥሏል።
