FDRE Ministry of Agriculture

የእርሻ መሳሪያዎችን በአግባቡ መጠቀም የሚያስችል የአቅም ግንባታ ስልጠና

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26/2018 (ግብርና ሚኒስቴር)‎ ግብርና ሚኒስቴር ከደቡብ ኮሪያ መንግስት ጋር በመተባበር የግብርና ሜካናይዜሽን የአቅም ግንባታ የአሰልጣኞች ስልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡

ሰልጣኞቹም ከዩኒቨርስቲዎች፣ ከኮሌጆች፣ ከምርምር ተቋማት እንዲሁም ከግል ተቋማት የተውጣጡ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ናቸው፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ሜካናይዜሽን መሪ ስራ አስፈፃሚ ሽመልስ ፀጋዬ ስልጠናው የእርሻ ማሽነሪዎች ጥገና፣ ዲዛይን እና ፍተሻ ላይ የሚያተኩር መሆኑን ገልፀው ይህም ስልጠና 11ኛው ዙር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ስልጠናው በንድፈ ሃሳብ እና በተግባር የታገዘ መሆኑን የገለፁት መሪ ስራ አስፈፃሚው ሰልጣኞች የግብርና ማሽነሪዎች ጥገና፣ ዲዛይን እና ፍተሻ ላይ ያላቸውን እውቀት እና ክህሎት የሚያሳድግ ነው ብለዋል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ በግብርና ሜካናይዜሽን ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎችን እውቀትና ክህሎት ይበልጥ ለማሳደግ አቅም ግንባታ ላይ ከበርካታ የልማት አጋር ድርጅቶች ጋር በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አቶ ሽመልስ አስረድተዋል፡፡

ሰልጣኞች ስልጠናውን በአግባቡ በመከታተል ያኙትን እውቀትና ክህሎት ለሌሎች በማካፈል ዘርፉን ለማሳደግ በሚደረገው ርብርብ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

ስልጠናው እየተሰጠ ያለው ከደቡብ ኮሪያ በመጡ የግብርና ሜካናይዜሽን ከፍተኛ ባለሙያዎች ሲሆን ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ አራት ቀናት ይቆያል፡፡

በተመሳሳይ በአዳማ ከተማ ከሁሉም ክልሎች እና ከድሬደዋ ከተማ መስተዳድር ለተውጣጡ በግብርና ሜካናይዜሽን ላይ ለተሰማሩ ባለሙያዎች የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኒካል ሰነድ አዘገጃጀት ላይ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡