FDRE Ministry of Agriculture

የኤክስፖርት ቄራዎችን አቅም ለማሳደግ ባለድርሻ አካላትን ማስተሳሰር!

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) በእንስሳት ልማት ኢንስቲትዮት አስተባባሪነት የወጪ ንግድ ቄራዎች፣ የሱማሌ ክልልና በኦሮሚያ ክልል የቦረና ዞን የእርድ እንስሳት ነጋዴዎች ማህበር አመራሮች የትስስር፣ ድርድርና የኮንትራት ስምምነት መድረክ እና በሞጆ ከተማ የሚገኙ የወጪ ንግድ ቄራዎችን በመጎብኘት የልምድ ልውውጥ አካሂደዋል።

የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አስራት ጤራ ዶ/ር የወጪ ንግድ ቄራዎች በአመት እስከ 200 ሺህ ቶን ስጋ ማምረት የሚያስችል አቅም ቢኖራቸውም አሁን ላይ ከ10 በመቶ እንደማይበልጥ ተናግረዋል።

ለዚህም ምክንያቱ የአቅርቦት ማነስ መሆኑን ጠቅሰው ይህንን ችግር ለመቅረፍ ሶስቱን ተዋናዮች አርብቶ አደሩን፣ ነጋዴውንና ቄራዎችን ማስተሳሰር ወሳኝ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም የወጪ ንግድ ቄራዎችን ምርት በቀጣይ ወደ 46 በመቶ ለማድረስ የሚታዮ ማነቆዎችን መፍታትና ተጨማሪ የዉጭ ሀገር ገበያ መዳረሻዎችን ለማስፋት ስፊ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው ነገር ግን የእንስሳት ዘርፍን ንግድ ለማሳለጥ በህገ-ወጦች ላይ ጠበቅ ያለ የአሰራር ስርዓት እንደሚያስፈልግ ዶ/ር አስራት ጠቁመዋል።

የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዮት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሳህሉ ሙሉ ዶ/ር ሀገራችን ያላትን የእንስሳት ሀብት በአግባቡ ወደ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለመቀየር በመንግስት በኩል በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አሁን ላይ 17 የወጪ ንግድ ቄራዎች እንደ ሀገር መኖራቸውን ጠቅሰው እነዚህ ተቋማት በአመት እስከ 10 ሚሊየን የእርድ እንስሳት ማምረት አቅም አላቸው ብለዋል።

ከአቅርቦት ማነስና በአንድ አንድ ማነቆዎች ምክንያት ከ3 ሚሊዮን እንደማይበልጥ ዶ/ር ሳህሉ ተናግረው የዛሬው ስምምነትና ህብረት መፈጠሩ ለዘርፉ እድገት ትልቅ አስተዋኦ ያበረክታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ስጋ አምራች እና ላኪዎች ማህበር ኘሬዝዳንት አቶ ከሊፋ ሁሴን በበኩላቸው የእርድ እንስሳት አቅራቢዎችና ቄራዎች ተቀራርበው መስራት መቻላቸው ችግሮችን በተደራጀ መንገድ በመፍታት ውጤታማ ስራ ለመስራት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

በመጨረሻም በእርድ እንስሳት አቅራቢዎችና የወጪ ንግድ ቄራዎች መካከል የስምምነት ፊርማ በማድረግ መድረኩ ተጠናቋል።