አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) የኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ከአጋሮቹ እንዲሁም ከሶማሌ ክልል ጋር በመተባበር ብሔራዊ የግጦሽ መሬት ጤና ክትትል ሲስተምን (NRMS) በይፋ አስጀምሯል።
ሲስተሙ በሳይንሳዊና ወቅታዊ የመረጃ አቅርቦት ላይ ተመስርቶ ዘላቂ የግጦሽ መሬትና የእንስሳት ሀብት አስተዳደርን ለመደገፍ እንዲሁም የአየር ንብረት ተጽዕኖን የመቋቋም አቅምን ለማጠናከር ያስችላል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት እና አጋሮቹ ሲስተሙን በተለያዩ አካባቢዎች በማስፋፋት በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን፣ በአፋር ክልል እና በድሬዳዋ አስተዳደር ዲዛይኑ ተጠናቅቆ በይፋ ተጀምሯል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፕሮፌሰር ፍሬው ተገኘ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት በሶማሌ ይፋ የሆነው የግጦሽ መሬት አያያዝና አጠባበቅ ሲስተም በተቀናጀ አስተዳደር፣ ቀጣይነት ባለው የባለድርሻ አካላት ተሳትፎና በጠንካራ ትብብር ላይ በመመሥረት ዘላቂ ለውጥ ማምጣት እንደሚችል ገልጸው ሁሉም አካላት ለተግባራዊነቱ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ በማበርከት የአርብቶ አደሩን ማኅበረሰብ ኑሮ ለማሻሻል በጋራ እንዲረባረቡ ጥሪ አቅርበዋል።
የሶማሌ የእንስሳትና ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ሸሪፍ በበኩላቸው፣ አስተማማኝ የግጦሽ መሬት መረጃ መኖሩ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የመሬት መራቆትና ወራሪ አረሞች በግጦሽ መሬቶች ላይ እያሳደሩት ያለውን ተጽዕኖዎች በማንሳት ይህ ሲስተም እነዚህን ችግሮች ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ለመካላከል ወሳኝ ነው ብለዋል።
የግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ወ/ሮ ፅጌረዳ ፈቃዱ እንደተናገሩት በብሔራዊ ደረጃ የተቀናጀና በሳይንሳዊ መሠረት የተደገፈ የክትትል ሥርዓት አስፈላጊነትን አስገንዝበዋል።
በመርሃ-ግብሩ የሲስተሙን ዲዛይንና ልማት በማካሄድ ላይ የተሳተፉ ባለሙያዎች ገለጻዎች ያቀረቡ ሲሆን በዚህም ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
