FDRE Ministry of Agriculture

የኢትዮጵያ የግብርና ሜካናይዜሽን ከየት ወደ የት?

የኢትዮጵያ ግብርና ከጥንት ጀምሮ የሕዝቡን ኑሮ ከመደገፍ ባለፈ ከፍተኛውን የሀገር ውስጥ ምርት ድርሻ እና የውጪ ንግድ ሲሸፍን ቆይቷል። የዘርፉ የምርታማነት እድገት ለዘመናት በሰውና በእንስሳት ጉልበት ላይ ብቻ በመመስረቱ ለኢንዱስትሪና ለውጭ ገበያ ተወዳዳሪ ምርት ማቅረብ አልተቻለም።

የኢትዮጵያ ግብርና ሜካናይዜሽን ታሪክ ከጥንታዊ የእርሻ መሳሪያዎች ጀምሮ እስከ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ድረስ ያካተተ ሲሆን በበሬ የሚጎተት ባሕላዊ ማረሻ ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ3ኛው ሺህ ዓመት ጀምሮ የሃገሪቱ ዋነኛ የእርሻ መሳሪያ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በመሆኑም የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አልፎ ለኢንዱስትሪና ለውጪ ንግድ በቂ ምርት ማቅረብ ያልቻለ ነበር።

ኢትዮጵያ የግብርና ሜካናይዜሽንን ከ1940ዎቹ አካባቢ ጀምሮ በወቅቱ የነበሩ የተለያዩ ትራክተሮችና ሌሎች የእርሻ መሳሪያዎችን ከውጭ በማስገባት በአንዳንድ ሰፋፊ የመንግስትና የግል እርሻዎች ላይ መጠቀም እንደጀመረች የታሪክ መዛግብቶች ይመሰክራሉ፡፡

በዚህም የኢትዮጵያ የግብርና ሜካናይዜሽን ታሪክ በሦስት ዋና ዋና ዘመናት ውስጥ ያለፈ ሲሆን ከ1942-1966 ዓ.ም እንደ ዱብቲ ባሉ አካባቢዎች በሜካኒካል ኃይል የሚንቀሳቀሱ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም እንደ አክሲዮን ማኅበር የሚንቀሳቀሱ ትላልቅ እርሻዎች ነበሩ።

ከ1966-1983 ዓ.ም የግብርና ሜካናይዜሽን በመንግሥት ባለቤትነት በተያዙ ሰፋፊ እርሻዎች ላይ ያተኮረ፣ በተማከለ እቅድ የተመራና የፋይናንስ እጥረት የነበረው በመሆኑ ዘላቂነት ሳይኖረው ቆይቷል፡፡

ከ1983 ዓ.ም ወዲህ ደግሞ ወደ ነፃ ገበያ በተደረገው ሽግግር የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እድገት ያሳየ ቢሆንም የግብርና ሜካናይዜሽን እድገት በአብዛኛው ያልተማከለ በተለይም በደጋማ እና ምርታማ አካባቢዎች ላይ ብቻ ያተኮረ ነበር።

ከለውጡ በኋላ የመደመር መንግሥት በግብርናው ዘርፍ በወሰዳቸው እርምጃዎች፤ የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ የበጋ መስኖ ስንዴ፣ የፋይናንስ ነፃነት እንዲሁም የግብርና ሜካናይዜሽንን ሥርዓታዊ ለማድረግ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል።

በዚህም የእርሻ ትራክተሮችን 27 ሺህ፣ አጭዶ መውቂያን 3000 እንዲሁም የመስኖ ፓምፖችን ከ500,000 በላይ ማድረስ የተቻለ ሲሆን ነገርግን የሀገሪቱ አጠቃላይ የሜካናይዜሽን ሽፋን አሁንም ዝቅተኛ ነው።

ምንም እንኳን ግብርናችን በሜካናይዜሽን አንዲደገፍ በማድረግ የማዘመኑ ሥራ እድገት እያሳየ ቢሆንም አብዛኛውን አነስተኛ አርሶ አደሮች በማካተት ተደራሽነቱን በሁሉም ክልሎች ከማስፋት አንጻር ገና ብዙ የሚቀረው ነው፡፡

የመደመር መንግስት የዓለም ግብርና በአሁኑ ወቅት የደረሰበትን ደረጃ በመረዳት የአርሶ አደሩን አስተሳሰብ በመቀየር፣ የገጠሩን ማህበረሰብ ማሸጋገር የሚችል የቴክኖሎጂ አቅርቦትና አጠቃቀም ሥርዓት በመዘርጋት ግብርናችን ወቅቱን የዋጀ እና የዘመነ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቷል፡፡

በግብርናው ሽግግር መሰረትም የግብርና ሜካናይዜሽን የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጠው በመሆኑ ዘመናዊ ማሽነሪዎችን ለአርሶና አርብቶ አደሮቻችን ማስታጠቅ ጊዜ የማይሠጠው ጉዳይ ነው፡፡

የሃገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች አነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ ዘመናዊ የእርሻ ማሽነሪዎችን እንዲገጣጥሙ፤ በሂደትም ወደ ማምረት እንዲገቡ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡

ምርምርን፣ ፈጠራን እና ሜካናይዜሽን ተኮር ሥልጠናንና ኤክስቴንሽንን እንዲሁም የፋይናንስ ተደራሽነትን ማስፋፋት፣ የመንግስት እና የግል አጋርነትን ማሳደግ፣ በሀገር ውስጥ ማምረት እና መገጣጠምን መደገፍ፣ የግብርና ሜካናይዜሽን የአገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ማቋቋምና ማስፋፋፈት፣ እንዲሁም የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂን በመጠቀም የጉልበት ድካምን ከመቀነስ ባሻገር ጊዜንና ወጪን በመቆጠብ ግብርናችንን የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዋልታ መሆኑን  ማስቀጠል የመንግስት የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው።

እየተስፋፋ የመጣውን የኩታ-ገጠም (ክላስተር) እርሻን አሁን ካለበት ደረጃ ለማሳደግ ግብርና ሜካናይዜሽን አጠቃቀምን ማስፋፋትና ለአምራቹ አርሶአደር ተደራሽ በማድረግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ሁሉም የግብርናው ዘርፍ ቤተሰብ በቅንጅት መስራት ለነገ የማይተው ጉዳይ ነው፡፡

አዘጋጅ፡- ሰለሞን ደምሰው

#ከማምረትበላይ

#BeyondProduction

————————-