FDRE Ministry of Agriculture

የኢትዮጵያ የዘር መረጃ ስርዓት ሥራ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8/2019 (ግብርና ሚኒስቴር)

‎የመረጃ አያያዝ ስርዓትን በማዘመን ፈጣንና ቀልጣፋ የግብዓት አቅርቦትን ለማሳደግ ግብርና ሚኒስቴር ከአጋርና ባለድሻ አካላት ጋር በመተባበር የተዘጋጀው «ኢትዮሲድ» የተሰኘ የዘር መረጃ ስርዓት ሥራ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ይፋ ተድርጓል።

‎ይህም እንደሀገር የተያዘውን የ2030 ዲጂታል አሠራር ግብ ከማሳካት አንጻር የምርጥ ዘር አቅርቦትን በዓይነትና በመጠን ተደራሽ በማድረግ ወደ ሙሉ ትግበራ ለመግባት ያስችላል።

‎የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ አበራ ለማ «ኢትዮሲድ» የተሰኘው የመረጃ ስርዓት የዘር ጥራትና አቅርቦትን በማሻሻል የግብርና ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ አኳያ ጉልህ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

‎ዘር የግብርና እምብርት ነው ያሉት አማካሪው ጥራት ያለው ዘር ለአርሶአደሩ ተደራሽ ለማድረግ፣ አስተማማኝ የመረጃ ስርዓት እጅግ ወሳኝ በመሆኑ ይህ የመረጃ ስርዓት ተዘጋጅቶ ይፋ መደረጉን ገልጸዋል።

‎የዚህን የምርጥ ዘር መረጃ አያያዝ ሥርዓት ዓላማ ዕውን ለማድረግ ክልሎች፣ የምርምር ተቋማት፣ ዩኒቨርስቲዎች፣ ዘር አባዢዎች፣ የግል ዘርፎችና አጋር አካላት በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ምን ዓይነት ምርጥ ዘር፣ መቼና የት እንደሚገኝ፣ ምን ያህል መጠንና በምን ያህል ዋጋ ማግኘት እንደሚችሉ ፈጣንና ቀልጣፋ መረጃ ተደራሽ በማድረግ የሀገሪቱን የዘር አቅርቦት ችግር ይፈታል ተብሏል።

‎የዓለምአቀፍ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት በኢትዮጵያ ተወካይ ናሙኮሎ ኮቪች (ዶ/ር) በበኩላቸው «ኢትዮሲድ» የምግብና ስርዓተ-ምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ሂደት የሀገሪቱን የመረጃ ስርዓት ወደ ትግበራ ያሸጋግራል ሲሉ ተናግረዋል።

‎በዛሬው ዕለት ይፋ የተደረገው «ኢትዮሲድ» የመረጃ ስርዓት ከሰብል ልማት ባሻገር የእንስሳት መኖን የመረጃ ስርዓት በማዘመን ከፍተኛ ሚና ስለሚኖረው የአረንጓዴ አሻራን እና የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቮችን ያስተሳስራል ብለዋል።

‎በዕለቱ «ኢትዮሲድ» (Ethio-Seed) የተሰኘ ድረ-ገጽ ይፋ የተደረገ ሲሆን በኢትዮጵያ ዲጂታል የዘር ስርዓት ላይ ትኩረት ያደረገ የመፅሐፍ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል፡፡

በመጨረሻም ለመርሃ-ግብሩ መሳካት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ዕውቅና ተሰጥቷል።