አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) በዛሬው ዕለት የግብርና ሚኒስቴር እና የተጠሪ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ሞዴል ፈፃሚዎች በተገኙበት “የኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነት ተስፋዎች፣ ፈተናዎች እና የቀጣይ አቅጣጫዎች!” በሚል መሪ ሃሳብ ላይ ውይይት ተደርጓል።

መንግስት በግብርናው ዘርፍ የተለያዩ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂ እና የህግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት የዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ደሳለኝ ተሻለ ተናገረዋል።
የሃገራችን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ላይ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች ለውጦች ማስመዝገባቸውንም ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል።
መንግስት የተለያዩ የልማት ኢኒሼቲቮችን በመቅረፅና ተግባራዊ በማድረግ ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት መንግስት ለግብርና ሜካናይዜሽን በሰጠው ትኩረት አበረታች ለውጥ ማስመዝገብ እንደተቻለም ሚኒስትር ዴኤታው አንስተዋል።
“የኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነት ተስፋዎች፣ ፈተናዎች እና የቀጣይ አቅጣጫዎች!” በሚል ርዕስ ለውይይቱ የመነሻ ፅሁፍ ያቀረቡት በግብርና ሚኒስቴር የፖሊሲ ጥናት መሪ ስራ አስፈፃሚ ተስፋዬ መንግስቴ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

የሃገራችን የምግብ ሉዓላዊነት ወቅታዊ ሁኔታዎችን፣ ተስፋዎችን እንዲሁም የቀጣይ አቅጣጫዎችን በተመለከት ባቀረቡት ፅሁፍ አብራርተዋል።
በምግብ ራስን መቻል አንድ ሃገር በመሰረታዊ የምግብ ሰብሎች ላይ የፍጆታ ፍላጎቷን፣ በግዥ ወይም ከውጭ በሚገባ የምግብ ምርት ላይ ሳይመሰረት የፍጆታ ፍላጎቷን በራስ አቅም የማሟላት አቅም መሆኑንም መሪ ስራ አስፈፃሚው በፅሁፋቸው አንስተዋል።
ሃገራችን ያላትን ዕምቅ ፀጋና የመልማት አቅም በአግባቡ መጠቀም፣ አመቺ የሆኑ የመንግስት ፖሊሲና ማዕቀፎችን በስፋት መተግበር፣ በዘርፉ የተመዘገቡ ስኬቶችን ማስቀጠል እና ሌሎች ምርታማነትን የሚያሳድጉ ተግባራትን ማከናወን የኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እንደሚያግዙ በፅሁፋቸው አብራርተዋል።

በግብርናው ዘርፍ በርካታ የሪፎርም ስራዎች እየተከናወኑ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ አንዱ “በመደመር መንግስት እይታ የግብርና እመርታ!” በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ቀጣይነት ያላቸው ስልጠናዎች ለዘርፉ አመራሮችና ሰራተኞች እየተሰጡ ይገኛሉ፡፡

ዘጋቢ፦ ሰለሞን ደምሰው
ፎቶ፦ ተክለመድህን አቻምየለህ
