ባለፉት አምስት ዓመታት መንግሥት ለእንስሳት ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረትና በነደፈው በሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ አማካኝነት በእንስሳት ምርትና ምርታማነት ላይ ተጨባጭና እምርታዊ ውጤቶች ተመዝግበዋል።
የወተት ምርታማነትን ለማሳደግ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻልና የማዳቀል አቅምን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ተችሏል። በተጨማሪም የአንድ ቀን ጫጩት ስርጭት፣ የዘመናዊ ቀፎ አቅርቦት፣ የዓሳ ጫጩት ስርጭት በስፋት በመሰራታቸው በዘርፉ አዲስ መነቃቃት ተፈጥሯል።

እነዚህ የተቀናጁ ጥረቶች በምርት እድገት ላይ በግልጽ የታዩ ውጤቶችን ያስመዘገቡ ሲሆን፣ በዜጎች የአመጋገብ ስርዓትና በምግብ ዋስትና ላይም አዎንታዊ ተጽዕኖ አሳርፈዋል። ለዚህም ማሳያ የሚሆነው የወተት ምርት በ2014 ዓ.ም ከነበረበት 5 ነጥብ 8 ቢሊዮን ሊትር ወደ 11 ነጥብ 7 ቢሊዮን ሊትር ማደጉ ነው።
በተመሳሳይ የእንቁላልና የዶሮ ስጋ ምርቶችም ትልቅ እመርታ ያሳዩ ሲሆን፣ የአንድ ቀን ጫጩት ስርጭት ከነበረበት 26 ሚሊዮን ወደ 131 ነጥብ 2 ሚሊዮን ከፍ ማለቱ የዘርፉ እድገት አንዱ ማሳያ ነው።

የንብ ሀብቱን ለማጠናከር በተከናወኑ ተግባራት የዘመናዊ ቀፎ አቅርቦት ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ወደ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን በማደጉ የማር ምርት ውጤት እንዲጨምር አስችሏል።

እነዚህን ስኬቶች በዘላቂነት ለማስቀጠልና ስራውን በተደራጀ መልኩ ለመምራት የወተት፣ የዶሮ፣ የማርና የዓሳ ልማት መንደሮች በተቀናጀ ሁኔታ ተመስርተዋል። መንደሮቹ የዝርያና የግብዓት አቅርቦትን ለማሳለጥ፣ የመኖ ልማትና የእንስሳት አመጋገብን ለማዘመን፣ የእንስሳት ጤና አገልግሎትን በተቀናጀ መልኩ ተደራሽ ለማድረግና አምራቹን በቀጥታ ከገበያ ጋር የሚያገናኝ ጠንካራ ትስስር ለመፍጠር ትልቅ ፋይዳ እያበረከቱ ይገኛሉ።
በአጠቃላይ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የሀገሪቱን የእንስሳት ሀብት ልማት ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገረ ስኬታማ ጉዞ መሆኑን በተግባር አሳይቷል።

አዘጋጅ፡- ባህሩ ሰጠኝ
