የኢትዮጵያ የምርጥ ዘር ፍላጎትና አቅርቦት ሂደት በመንግሥት ተቋማት፣ በዩኒየኖች፣ በኅብረት ሥራ ማህበራት እንዲሁም በግል ዘር አምራቾችና አከፋፋዮች ተሳትፎ የሚከናወን ቢሆንም፣ ወቅታዊ እና የተሟላ መረጃ ውስንነት ትልቅ ፈተና ሆኖ ቆይቷል።
እስከ አሁን ባለው ሁኔታ በተለያዩ የዘር ተዋናዮች የሚመረተውንና የሚቀርበውን የምርጥ ዘር መረጃ በወቅቱና በተደራጀ መልኩ ለማግኘት፣ በተለይም የመነሻ ዘር እና የተመሰከረለት ዘር ፍላጎትና አቅርቦትን ዝርዝር መረጃ ለይቶ ማወቅ አስቸጋሪ ነበር።
በተጨማሪም በየዓመቱ በምርጥ ዘር ምርትና ግብይት ላይ የሚሳተፉ አካላትን ቁጥርና የአፈጻጸም ሁኔታ በተሟላና ወጥ በሆነ መልኩ ለመከታተል ሰፊ የመረጃ ክፍተት የነበረ በመሆኑ፣ ዘርፉን በጥራት ለመምራት ሲፈታተን ቆይቷል።
ይህንን ዘመናት የተሻገረ የዘር መረጃ ክፍተት በዘላቂነት ለመፍታት ግብርና ሚኒስቴር ከዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ጋር በመተባበር «ኢትዮሲድ» የተሰኘ ዲጂታል የመረጃ ሥርዓት አበልጽጎ ወደ ሥራ አስገብቷል።
ይህ ዲጂታል የምርጥ ዘር መረጃ ሥርዓት በዓለምአቀፍ የልማት አጋር አካላት የቴክኒክና ፋይናንስ ድጋፍ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በልጽጎ፣ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ደህንነቱ ተረጋግጦ፣ ግብርና ሚኒስቴር በባለቤትነት ተረክቦታል፡፡
አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተሞችን ጨምሮ ለሁሉም ክልሎች የግብርና ግብዓት ዳይሬክተሮችና ባለሙያዎች የአሰልጣኞች ስልጠና ከተሰጠ በኋላ ነው መስከረም 8 ቀን 2019 ዓ.ም በይፋ ሥራ የጀመረው።
«ኢትዮሲድ» የዘር ፍላጎት፣ ብዜት፣ አቅርቦትና ሥርጭት የተዋናዮችን መረጃ በዲጂታል መንገድ ለመመዝገብና ለማደራጀት የሚያስችል ሲሆን አፈጻጸሙን በወቅቱ ለመከታተልና በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርቶ ወቅታዊ ውሳኔዎችን ለማስተላለፍ ትልቅ አቅም ይፈጥራል።
የመረጃ ሥርዓቱ ትግበራ በተሳካ ሁኔታ እየቀጠለ ሲሆን፣ ሁሉም ክልሎች የመረጃ መመዝገቢያ ሥርዓቱን ለመጠቀም የሚያስችል ፍቃድ (Access Admin) ከግብርና ሚኒስቴር አይ.ሲ.ቲ ሥራ አሥፈጻሚ በማግኘት በሚወክሏቸው ባለሙያዎች አማካኝነት የየክልላቸውን የምርጥ ዘር ፍላጎትና የምርት መረጃ በየጊዜው ወደ ኢትዮሲድ ዲጂታል ሥርዓት የሚያስገቡ ይሆናል። የዘር መረጃ ፈላጊዎችም በ https://ethioseed.moa.gov.et/ ከፍተው ማየት ይችላሉ፡፡
«ኢትዮሲድ» የምርጥ ዘር መረጃን በአንድ ማዕከል በማደራጀት ፍላጎትና አቅርቦት በወቅቱ ለማወቅ፣ የዘር ተዋናዮችን ተሳትፎ በጥብቅ ለመከታተል እና በተሟላና ተዓማኒ መረጃ ላይ የተመሰረተ ዕቅድና ውሳኔ ለማሳለጥ የሚያስችል ወሳኝ የዲጂታል መሣሪያ ሆኖ ያገለግላል።
ይህ የመረጃ ሥርዓት ማነቆዎችን ለመለየት፣ ተዓማኒ መረጃ በማመንጨት፣ ዘላቂ መፍትሔዎችን ለማመቻቸት፣ የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፎችንና ጥናቶችን ለማካሄድ የጎላ ሚና የሚጫወት ይሆናል፡፡
