ሀይድሮፖኒክ ከግሪክ ቃል የተገኘ ሲሆን “ሀይድሮ” (ውሃ) እና “ፖኒክ” (ስራ) ማለትም “በውሃ የሚሰራ” ማለት ነው። ይህ ቴክኖሎጂ በሆላንድ፣ ጀርመን፣ አውስትራሊያ፣ እና በጎረቤት ሀገር ኬኒያ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል። አሁን ደግሞ በሀገራችን በተሳካ ሁኔታ እየተተገበረ ነው፡፡
የአፈር አልባ አረንጓዴ መኖ (Hydroponics) በዘመናዊ የእንስሳት እርባታ ውስጥ ትልቅ አቢዮት እየፈጠረ ይገኛል። ከድርቆሽና የሰብል ተረፈ ምርት የበለጠ ተመራጭ ሲሆን በተለይም በበጋ ወቅት ተፈጥሯዊ ግጦሽ በሚጠፋበት ጊዜ ከፍተኛ የፕሮቲንና የቪታሚን አማራጭ በመሆን ለወተት ላም፣ ለእንስሳት ማድለብ እና ለዶሮ እርባታ የላቀ ጠቀሜታ አለው።
ይህ አስደናቂ ቴክኖሎጂ በተፈጥሮ አፈር ላይ የሚወስደውን የመኖ ልማት ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ በማሳጠር ከ7 እስከ 10 ቀናት ውስጥ ከፍተኛ ምርት ለመሰብሰብ ያስችላል።
አነስተኛ ዘርን ወደ ላቀ የአረንጓዴ መኖ መጠን በመቀየር የመኖ ምርታማነትን ከ1 ኪሎ ግራም የገብስ ዘር ከ6 እስከ 10 ኪሎ ግራም አረንጓዴ መኖ ከማሳደጉም በላይ የእንስሳትን የመራባት አቅምና ጤንነትን በማሻሻል የወተት፣ የስጋ እና የእንቁላል ምርትን በከፍተኛ ደረጃ ያሳድጋል።
በተጨማሪም መኖው በፕሮቲን የበለጸገ በመሆኑ የእንስሳትን የእለት ተእለት የውሃ ፍጆታ በጥሩ ሁኔታ ለመቀነስ ይረዳል።
ለመኖ ማምረቻነት ገብስ፣ ስንዴና በቆሎን መጠቀም የሚቻል ቢሆንም የደረቅ መኖ መጠኑ 88 በመቶና የፕሮቲን መጠኑ 12 በመቶ የሆነው የገብስ ዘር ይበልጥ ተመራጭ ነው፡፡
የሚያስፈልጉ ዋና ዋና ግብዓቶች የማዕድን ውህድ፣ የማምረቻ ትሪና ፕላስቲክ ሽት፣ የፕላስቲክ ባልዲ፣ ንጹህ ዘር (የገብስ፣ ስንዴ፣ በቆሎ)፣ የውሃ ማጠጫ እቃ እና የጽዳት ፈሳሾች ናቸው፡፡
የምናመርተው መኖ ስሩ፣ ቅጠሉና ያልበቀለው ዘር ጭምር ሙሉ በሙሉ ስለሚበላ ንጽህናውን መጠበቅና ሻጋታ እንዳይፈጠር ማድረግ ወሳኝ ነው፡፡ ጥራት የሌላቸውንና ወደ ላይ የሚንሳፈፉትን ዘሮችና ባዕድ ነገሮች ማስወገድ እና ዘሩን ከ2 እስከ 3 ጊዜ በንፁህ ውሃ በደንብ ማጠብ ያስፈልጋል፡፡
በተከታታይ ከ7 እስከ 10 ቀናት ውስጥ የሚሰሩ ተግባራት ቅደም-ተከተል
1ኛ ቀን:- ዘሩን መምረጥና መዘፍዘፍ
ዘሩን መምረጥ፣ ማበጠርና ማጽዳት፣ በንፁህ ውሃ እና በትንሽ የሳሙና ጠብታ 2 እና 3 ጊዜ ማጠብ፣ በንጹህ ውሃ ከ3 እስከ 4 ሰዓት መንከር፤ በመጨረሻው 1 ሰዓት ላይ በረኪና (1 ሚሊ ሊትር በረኪና 1 ሊትር ውሃ) ጨምሮ መዘፍዘፍ፣ አውጥቶ በማንጣፈፍ አየር በማያስገባ እቃ ውስጥ ለ24 ሰዓት በጨለማ ክፍል ማስቀመጥ፡፡
2ኛ ቀን:- መዝራት
የበቀለውን ዘር በማብቀያ ትሪ ላይ ወጥነት ባለው መልኩ መዝራትና ንፁህ ውሃ በማጠጣት ለተጨማሪ 24 ሰዓት ማቆየት፡፡
ከ3ኛ እስከ 7ኛ ቀን:- የማዕድን ውሃ ማጠጣት
የተዘጋጀውን የማዕድን ውህድ እንደ አየሩ ፀባይ በቀን ከ2 እስከ 3 ጊዜ (በየ4 ሰዓት ልዩነት) ማጠጣት መጀመር፡፡
ከ7ኛ እስከ 10ኛ ቀን:- ምርት መሰብሰብ
ያደገውን አረንጓዴ መኖ በጥራት በመሰብሰብ ለእንስሳት መመገብ (በቀን ለዳልጋ ከብት ከ6 እስከ 8 ኪሎ ግራም፣ ለጎች እና ፍየሎች 1 ኪሎግራም፣ ለዶሮዎች ከ80 እስከ 100 ግራም መመገብ ያስፈልጋል፡፡
