
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከንባታ ጠምባሮ ዞን ቃጫ ቢራ ወረዳ የምትገኘው ዌሬራማ ቀበሌ በምቹ አየር ንብረቷ በርካታ አርሶ አደሮችን ይዛ የምግብና ስርዓተ-ምግብ ዋስትን ለማረጋገጥ እንዲሁም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ዘላቂ ግብርናን ለመገንባት በስራ ላይ ትገኛለች፡፡ አርሶ አደሮቿ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ጠዋት ማታ በእርሻ ማሳቸው ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ትጉህ አርሶ አደሮች መካከል አንዱ አርሶ አደር ደስታ ሀንፎሬ ናቸው፡፡

አርሶአደር ደስታ ለበርካታ ዓመታት በንግድ ስራ ተሰማርተው ቆይተዋል፡፡ በዌሬራማ ቀበሌ የሚገኘው 3.5 ሄክታር መሬታቸው ለበርካታ አመታት በባህር ዛፍ ተሸፍኖ ቆይቷል፡፡ ከሦስት ዓመታት በፊት አርሶ አደር ደስታ የወሰኑት ውሳኔ ግን የራሳቸውን ኑሮ ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው የግብርና ልማትም ትልቅ ተሞክሮን አስገኝቷል። መሬታቸው በአብዛኛው በባሕር ዛፍ የተሸፈነ ቢሆንም መሬቱ ከዚህ የበለጠ የኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚያስገኙ የፍራፍሬና የቡና ሰብሎችን ለማምረት ተስማሚ መሆኑን ተገንዝበው አዲስ ጉዞ ጀመሩ።

በዚህም የነበሩትን ባሕር ዛፎችን በማስወገድ በሙዝ፣ ሮዝመሪ፣ ቡናና አቮካዶ ልማት ተክተው መሬታቸውን ወደ ከፍተኛ ምርታማነት ቀይረውታል። በተጨማሪም የፍራፍሬና የቡና ችግኝ ማፍላት በመጀመር ለመንግሥት ተቋማትና ለአካባቢው ማህበረሰብ ጥራት ያለው ችግኝ ማቅረብ ጀምረዋል።
መሬቱ ድንጋያማና ተዳፋት በመሆኑ ለምነቱን ለመቀየር የሰሩት ስራ ቀላል እንዳልሆነ የሚናገሩት አርሶአደር ደስታ በርካታ ኩንታል የቡና ገለባ እና ኮምፖስት በማስደፋት መሬቱን ለፍራፍሬና ቡና ልማት ምቹ እንዲሆን ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ በባሕር ዛፍ ተሸፍኖ የነበረው መሬት በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ውብና ምርታማ የሙዝ፣ የአቮካዶና የቡና እርሻ ተቀይሯል። የመሬት ዝግጅት፣ የችግኝ ጣቢያ ማቋቋም፣ የተሻሻሉ ዝርያዎችን መትከል፣ ትክክለኛ እንክብካቤ ማድረግ እና የግብርና ባለሙያዎች የሚሰጧቸውን ምክረ-ሀሳቦች በመተግበር ውጤታማ ሥራ እያከናወኑ ይገኛሉ።

በዚህ አመት በዋናነት 26 ሺህ 700 ጥራት ያለው የሙዝ ችግኞችን ለአካባቢው አርሶ አደሮችና ለመንግስት ተቋማት እያቀረቡ ሲሆን ከዚህ ባለፈ የሙዝ ምርት በስፋት እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡ በዚህም በአካባቢው የእሳቸውን ተሞክሮ የሚከተሉ አርሶ አደሮች ብቅ ብለዋል፡፡
ባሕር ዛፍን በፍራፍሬና በቡና ልማት መተካታቸው የተሻለ የመሬት አጠቃቀምን በማስፈን የተፈጥሮ ሀብት አጠባበቅንና የምግብ ዋስትና ስራቸውን አጠናክሮላቸዋል።
“ባሕር ዛፉን አንስቼ በፍራፍሬና በቡና ልማት ለመተካት ስወስን ብዙዎች ለምን ይህን ታደርጋለህ እያሉ ጠይቀውኝ ነበር” ያሉት አርሶ አደር ደስታ ዛሬ ግን የፍራፍሬና የቡና ልማት ከፍተኛ ገቢ እንደሚያስገኝ፣ ለሌሎችም የሥራ እድል እንደሚፈጥር ሁሉም እያዩ ስለሆነ በዚህ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደር ደስታ የፍራፍሬ ችግኝ እና ምርቱን ለገበያ በማቅረብ ለራሳቸው ከሚያገኙት ገቢ ባለፈ ለ15 ቋሚና ከ20-25 ለሚሆኑ ጊዚያዊ የስራ እድል በመፍጠር ማህበራዊና አካባቢያዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ነው፡፡ ልማታቸውን የወንዝ ውሃ በመጥለፍና ኩሬ በመስራት የሚያለሙ በመሆኑ ይህን ለማጠናከር፣ ለማቀላጠፍና ምርትና ምርታማነቱን ለማብዛት በወንዙ በቂ ውሃ ቢኖርም በፓምፕ ወደ ማሳው ለማምጣት ግን የሶላር ፓምፕ ችግር እንዳጋጠማቸው ገልፀውልናል፡፡
በቀጣይ የፍራፍሬ ምርቶችን በማቀነባበር ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ገበያ የማቅረብ አላማን ሰንቀው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
አዘጋጅ፡- ተዋበ ጫኔ
ፎቶግራፈር፡- ጌታቸው ምትኩ
