FDRE Ministry of Agriculture

የአካታች እና ዘላቂ የግብርና እሴት ሰንሰለት ልማት ፕሮጀክት ትሩፋት!

ሀዋሳ፣ ግንቦት 13/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) በግብርና ሚኒስቴር የአካታች እና ዘላቂ የግብርና እሴት ሰንሰለት ልማት ፕሮጀክት መንግስት አርሶአደሩን ከበሬ ወደ ትራክተር ለማሸጋገር እያከናወነ ያለውን ተግባር በመደገፍ 120 የፈረስ ጉልበት ያላቸው 10 ትራክተሮችን ለሲዳማ ክልል አስረክቧል።

የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ መምሩ ሞኬ በርክክብ ሥነ ስርዓቱ ላይ ፕሮጀክቱ በክልሉ 10 ወረዳዎች ለ200 ሺህ ተጠቃሚዎች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በማሳደግ፣ የፍራፍሬ ችግኞችን በማልማት፣ የሥራ ዕድል እና የገበያ ትሥሥርን በመፍጠር፣ ሜካናይዜሽንና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን በማስፋፋት ለክልሉ ዕድገት ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ እንደ አቮካዶ ያሉ የግብርና ምርቶችን ለይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ተደራሽ በማድረግ የአርሶአደሮችንና የማህበራትን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል።

የአካታች እና ዘላቂ የግብርና እሴት ሰንሰለት ልማት ፕሮጀክት ብሔራዊ ማናጀር ሰለሞን ዳኜ ፕሮጀክቱ አርሶአደሮችንና ማህበራትን ከተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ጋር በማስተሳሰር ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ አርሶአደሩን ከባህላዊ የእርሻ አሠራር ወደ ዘመናዊ ሜካናይዜሽን ለማሸጋገር እንዲሁም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት እየተደረገ ላለው ርብርብ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ብሔራዊ አስተባባሪው አብራርተዋል።

ዘጋቢ፦ ባህሩ ሰጠኝ

ፎቶ፦ ዮዲት እንዳለው