FDRE Ministry of Agriculture

የአበባ ኢንቨስትመንት አሁን ካለበት 1 ሺህ 750 ሄ/ር ወደ 3 ሺህ ሄ/ር መሬት ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ ነው

ወልቂጤ፣ ሚያዚያ 7/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) ግብርና ሚኒስቴር ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እና የሆርቲካልቸር አምራች ላኪ ማህበር ጋር በመተባበር በጉራጌ ዞን ለሆርቲካልቸር ኢንቨስትመንት የተዘጋጀ የመሬት አቅርቦት ለባለሃብቶች የማመቻቸት መርሃ ግብር አካሂዷል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ኢንቨስትመንትና ምርት ግብይት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ደረጀ አበበ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከክልል መንግስታት ጋር በመቀናጀት ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ የሆርቲካልቸር አምራች ላኪ ባለሃብቶች መሬት የማስተላለፍ ስራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሆርቲካልቸር ኢንቨስትመንት በዓመት ከግማሽ ቢሊየን በላይ የውጭ ምንዛሬ እያስገኘ መሆኑን የገለፁት መሪ ስራ አስፈፃሚው፣ ከ200 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል የፈጠረ ንዑስ ዘርፍ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በቀጣይ ሶስት ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ የአበባ ኢንቨስትመንት አሁን ካለበት 1 ሺህ 750 ሄ/ር ወደ 3 ሺህ ሄ/ር መሬት ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አንስተው፣ ለአብነትም የአበባ ኢንቨስትመንት ለማካሄድ ከታቀደባቸው ክልሎች መካከል ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አንዱና ዋናው ነው ብለዋል፡፡

የሆርቲካልቸር ኢንቨስትመንት በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ኃላፊነት የተሞላበት ማህበራዊ ድጋፎችን በማድረግ ከየትኛውም የኢንቨስትመንት አማራጭ የተሻለ እንደሆነ ጥናቶች እንደሚያመላክቱ አቶ ደረጀ ጠቅሰው ኢንቨስትመንቱ ለጉራጌ ዞን ልማት ፋይዳው የላቀ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አባስ መሃመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው ክልሉ ለሆርቲካልቸር ኢንቨስትመንት አመቺ መሆኑን ገልፀው፣ ባለሃብቶች በሆርቲካልቸር ልማት መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዞኑ ከ1 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በሆርቲካልቸር የማልማት አቅም ያለ ሲሆን በአሁኑ ወቅት 500 ሄ/ር መሬት ለባለሃብት ለማስተላለፍ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጉራጌ ዞን ለሆርቲካልቸር ኢንቨስትመንት ያሉ መልካም ዕድሎችን የሚዳስስ ሰነድ ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡

በመጨረሻም በጉራጌ ዞን ለሆርቲካልቸር ኢንቨስትመንት ለማስተላለፍ የተዘጋጁ መሬቶች ላይ የመስክ ጉብኝት የተካሄደ ሲሆን ለባለሃብቶቹ በክልሉ እና በዞኑ ኃላፊዎች ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

ዘጋቢ፡- ዮሐንስ ደመቀ

ፎቶግራፈር፡- ጌታቸው ምትኩ