የአርብቶአደር ምግብና ስርዓተ-ምግብ ማሻሻያ ፕሮጀክት የድርቅ መቋቋሚያና ዘላቂ የአርብቶአደር ኑሮ ማሻሻያ ፕሮግራም/Drought Resilience and Sustainable Livelihoods Program (DRSLP) ቀጣይ ክፍል ሲሆን ከ2014 ዓ.ም ነሐሴ ወር ጀምሮ እስከ 2020 ዓ.ም ታህሳስ ወር ድረስ በኦሮሚያ፣ አፋር፣ ሶማሌ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች በሚገኙ አርብቶአደር አካባቢዎች ውስጥ በተመረጡ 30 ወረዳዎች እና 240 ቀበሌዎች ላይ ከ2.07 ሚሊዮን በላይ ለሚገመቱ አርብቶአደሮች ድጋፍ እያደረገ የሚገኝ ፕሮጀክት ነው፡፡

ከእነዚህም ተጠቃሚዎች ውስጥ 50 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው። ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ 46 ሚሊዮን ዶላር በጀት የተያዘ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 86.9 በመቶ ከአፍሪካ ልማት ባንክ፣ 8.8 በመቶ ከኢትዮጵያ መንግስት እንዲሁም 4.3 በመቶ ከማህበረሰብ አስተዋጽኦ በተገኘ ድጋፍ እየተተገበረ ይገኛል።

የአርብቶ አደር ምግብና ስርዓተ-ምግብ ማሻሻያ ፕሮጀክት ዋና ዓላማ የአርብቶ አደር ማህበረሰብ የሆኑ ሴቶች፣ ወጣቶችና የአደጋ ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን የኑሮ ሁኔታን ማሻሻል፣ የምግብና የስነ-ምግብ ደህንነትን ማጠናከር እንዲሁም ድርቅን የመቋቋም አቅምን ማሳደግና ማጠናከር ነው።
የአርብቶ አደር ምግብና ስርዓተ-ምግብ ማሻሻያ ፕሮጀክት በሶስት ዋና ዋና ክፍሎች እና በፕሮግራም ማስተባበሪያና አስተዳደር ላይ የተለያዩ ዋና ዋና ተግባራትን በማከናወን አመርቂ ውጤቶችን እያስመዘገበ ይገኛል፡፡
በዚህም የአርብቶና ከፊል አርብቶአደር ምርት ስርዓቶችን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በማቀናጀት የመቋቋም አቅምን ማጠናከር ሲሆን ፕሮጀክቱ በዚህ ክፍል ለሰው፣ ለእንስሳት እና ለመስኖ ልማት የሚውል የውሃ አቅርቦት ላይ ያከናወነው ስራ አበረታች ነው፡፡

አዲስና ነባር አነስተኛ የውሃ መሰረተ-ልማት ግንባታና ጥገና ላይ ብዙ ስራዎችን ሰርቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የመጋቢ መንገድ ግንባታ እና አነስተኛ ድልድይ የሰራ ሲሆን የእንስሳት ገበያ ማዕከል የመገንባት ስራም አከናውኗል፡፡
የእንስሳት ጤና መሰረተ-ልማት ማለትም የእንስሳት ጤና ኬላ ግንባታ፣ የእንስሳት ጤና ክሊኒክ፣ የእንስሳት መኖ መጋዘንና ተንቀሳቃሽ የእንስሳት ጤና ክሊኒክ/አምቡላንስ እና ዘላቂ የአርብቶ አደር አካባቢ የመሬት አስተዳደር ድጋፍ የተፈጥሮ ግጦሽ ልማትና ማስተዳደር እና የተቀናጀ የእንስሳት መኖ ልማት ላይ ስኬታማ ስራዎችን አከናውኗል፡፡

በተጨማሪም ለወጣቶችና ለሴቶች የአግሪ-ቢዝነስ ልማትን በመደገፍ ወደ ሥራ እንዲገቡና ኑሯቸው እንዲለወጥ እያደረገ ይገኛል፡፡ ከዚህ ውስጥ የወተት ማሰባሰብ ማዕከላት የተገነቡ ሲሆን የተለያዩ አግሪ ፕሪነሮች በዶሮ እርባታ፣ በንብ ማነብ፣ በፍየል ማሞከት፣ በዓሳ ልማት እና በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ማህበራት ተደራጅተው ውጤት አስመዝግበዋል፡፡

ፕሮጀክቱ የአርብቶ አደር ህብረተሰብ አቅምን በማጠናከር የአየር ንብረት ለውጥ እንዲቋቋም ማስቻል ሲሆን ከኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር አውቶማቲክ አግሮ-ሜትሮሎጂካል ማዕከላትን የማቋቋም ስራዎችንም እየሰራ ይገኛል፡፡
