ተገቢ የሆነ ተግባራዊ የግብርና እውቀት፣ ሙያዊ ምክርና የተሻሻሉ የምርት ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ማድረግ ለምርታማነት መሻሻል ወሳኝ ሚና አለው። አርሶ አደሩ የግብርና ስራዎችን ከእርሻ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ድህረ-ምርት ያሉትን ሂደቶች ተረድተው እንዲተገብሩ የአርሶ አደር ማሰልጠኛ ማዕከላት አስተዋፅኦ የጎላ ነው፡፡


አርሶ አደር ክፍሌ መንገሻ እና አርሶ አደር ሊዲያ ዳንኤል በጌዲኦ ዞን ገደብ ወረዳ ገደብ ጎልቻ ቀበሌ ነዋሪዎች ሲሆኑ ሞዴል የአርሶ አደር ማሰልጠኛ ማዕከል በመጠቀም የተሻሻለ የምርት አሰራርን በመተግበር ውጤታማ ለውጥ ካመጡ አርሶ አደሮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
በገደብ ጎልቻ ቀበሌ የሚገኘው ሞዴል የአርሶ አደር ማሰልጠኛ ማዕከል በ2.5 ሄክታር መሬት ላያ ያረፈ ሲሆን ከተመሰረተ 2 አመታትን አስቆጥሯል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ከ850 በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እያደረግ የሚገኘው ማዕከሉ ለአርሶ አደር ክፍሌ እና አርሶ አደር ሊዲያ አስፈላጊውን የግብርና ተግባራዊ እውቀት፣ ሙያዊ ምክርና የተሻሻሉ የምርት ቴክኖሎጂዎችን እያቀረበላቸው ይገኛል፡፡
ማዕከሉ ከመመስረቱ በፊት የአካባቢው አርሶ አደር ባህላዊ የእርሻ አሰራር፣ የቴክኒክ እውቀት ክፍተት፣ የግብዓት አጠቃቀም ችግር እና ዝቅተኛ ምርታማነት ይገጥመን ነበር ያሉን አርሶ አደር ሊዲያ፣ አሁን ላይ የቀበሌውና አጎራባች አርሶ አደሮች በመሰባሰብ ከፍተኛ የስነ-ምግብ ይዘት እና የገበያ ዋጋ ያላቸው የሰብል፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ስልጠናዎችን በመውሰዳቸው የምግብ እና ስነ-ምግብ ዋስትናቸውን እያረጋገጡ መሆናቸውን ገልጻዋል፡፡

በማሰልጠኛ ማዕከሉ በተሰጠው ተከታታይ ስልጠና እና በተግባራዊ የማሳ ላይ ሰርቶ ማሳያዎች አማካኝነት የተሻሻለ የዘር አመራረጥ፣ ተገቢ የመሬት ዝግጅት፣ ትክክለኛ የዘር አሰራር፣ የማዳበሪያ አጠቃቀም፣ የተባይና በሽታ ቁጥጥር፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ ወቅታዊ የምርት አሰባሰብ እና ሌሎች የተሻሻሉ የምርት አሰራሮችን ተምረን በእርሻ ማሳችን እየተገበርን ነው ያሉት አርሶ አደር ክፍሌ መንገሻ ደግሞ ከማዕከሉ ትምህርት በመውሰድ ከዚህ በፊት ያልሞከሩትን የጓሮ አትክልት ልማት እያለሙ ለልጆቻቸው የተመጣጠነ ምግብ ከማቅረብ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

“ማዕከሉ ምን መስራት እንዳለብኝ ብቻ ሳይሆን ስራውን መቼና እንዴት መተግበር እንዳለብኝ አስተምሮኛል” ያሉት አርሶ አደር ክፍሌ፣ ያገኙትን እውቀት በግል ማሳቸው በመተግበር ምርትና ምርታማነታቸውን ከማሳደግ ባለፈ ሌሎች አርሶ አደሮች እንዲጠቀሙ ተሞክሯቸውን እያካፈሉ ይገኛሉ፡፡
የአርሶአደር ማሰልጠኛ ማዕከሉ ለአርሶአደሩ እውቀት፣ ክህሎት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ተግባራዊ ስልጠና፣ ሰርቶ ማሳያ እና የቴክኒክ ምክር የሚሰጥ የግብርና እውቀት እና ቴክኖሎጂ ማዕከል ሆኖ እያገለገለ ነው፡፡ ማዕከሉ በቀጣይ የአርሶ አደሩን ምርታማነት፣ ገቢ እና የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል አሰራሩን ዲጂታላይዝ የማድረግ ስራ ጀምሯል፡፡
