FDRE Ministry of Agriculture

የአርሶአደሮች ማሰልጠኛ ማዕከላትን የማዘመን ንቅናቄ በሲዳማ ክልል!

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17/2018 ዓ.ም (ግብርና ሚኒስቴር) በሲዳማ ክልል የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለፈጣን የግብርና ሽግግር መሰረት የሆኑ  የአርሶ አደሮች ማሰልጠኛ ማዕከላትን የማዘመን እና የቀበሌ የግብርና ባለሙያዎችን አቅም የመገንባት ስራዎችን በትኩረት እያከናወነ ይገኛል፡፡

ማሰልጠኛ ማዕከላቱ አርሶ አደሮች በተግባር የሚማሩበት፣ የአሰራርና አተገባበር ማነቆዎች የሚፈቱበት፣ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎች ወደ አርሶ አደሩ የሚሸጋገሩበት ነው፡፡

የግብርና ሽግግሩን ለማፋጠን በምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ድጋፍ በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይ፣ ሲዳማ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች የአርሶ አደሮች ማሰልጠኛ ማዕከላትን የማዘመን ንቅናቄ በ2017 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን በሲዳማ ክልል ማዕከሎቹን በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የማጠናከር እንዲሁም የባለሙያዎቹን አቅም የማጎልበት ተግባር በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡

በክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ የኤክስቴንሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ለማ ዋቃዮ እንደገለፁት፣ ማዕከላቱን የማዘመን ንቅናቄው ከተጀመረ ወዲህ 7 የአርሶ አደሮች ማሰልጠኛ ማዕከላትን ማዘመን ተችሏል፡፡ የእነዚህ ማዕከላትን ተሞክሮ በማስፋፋት ሌሎችንም የማዘመን ስራ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡

የአርሶ አደሮች ማሰልጠኛ ማዕከላትን ከማዘመን ጎን ለጎን አምና እና ዘንድሮ 1 ሺህ 830 የሚሆኑ የቀበሌ የግብርና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና ማግኘታቸውን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፣ በዚህ አመት በግብርና ሚኒስቴር ድጋፍ 448 ባለሙያዎች ከደረጃ 2 ወደ ደረጃ 4 የሚያሳድጋቸውን ስልጠና በተለያዩ ተቋማት እየወሰዱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ቅድሚያ የመዘመን እድል ካገኙት ማዕከላት መካከል በማልጋ ወረዳ የሚገኘው ቆቾ የአርሶአደሮች ማሰልጠኛ ማዕከል አንዱ ሲሆን እንደ ወረዳ ወቅቱ የሚጠይቀውን መስፈርቶች አሟልቶ የተመረጠ ነው፡፡ አሁን ላይ ደረጃቸውን የጠበቁ የአርሶ አደሮች ማሰልጠኛ ክፍል፣ ቢሮዎችና ሽንት ቤት ተገንብተውለታል፡፡ ማዕከሉ ዙሪያውን በሽቦና በብረት የታጠረ ሲሆን ለዲጂታል ግብርና መሰረት የሆነው ዲጂታል ሲስተም ገብቶለታል፡፡

በግንባታው ሂደት የታየውን የጥራት ጉድለት በክትትልና ድጋፍ ስራዎች የጥራት ጉድለቱ እንዲስተካከል እየተደረገ መሆኑንም አቶ ለማ አብራርተዋል፡፡

የማልጋ ወረዳ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሸናፊ አለማየሁ በበኩላቸው ለማዕከሉ ክትትልና ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመው፣  የተሰሩ ስራዎች እንዳሉ ሆነው የጎደሉትን ለማሟላት ከክልሉ ጋር ተናበን እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

ማዕከሉ የእርርሻ፣ የሆርቲካልቸር፣ የእንስሳትና የተፈጥሮ ሀብት ስራዎችን አቀናጅቶ የያዘ ሲሆን አርሶ አደሮችም በወር 1 ጊዜ ወደ ማዕከሉ በመምጣት በሰርቶ-ማሳያ ማሳዎች ጉብኝትና ውይይት እንደሚያደርጉ የገለፁት ኃላፊው፣ በማዕከሉ ያለውን ተሞክሮ ወደ ሌሎች ማዕከላት ለማስፋፋት አቅደው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ቆቾ የአርሶ አደሮች ማሰልጠኛ ማዕከል ቦታው ዳገታማ ሲሆን ስፋቱ 3.14 ሄክታር ነው፡፡ ከቆቾ ቀበሌ ውጪ ላሉ ቀበሌዎችም የስልጠና አገልግሎት የሚሰጥ ሞዴል ማዕከል ነው፡፡

በማዕከሉ ለሰርቶ-ማሳያነት የተለያዩ ሰብሎች ይለማሉ፡፡ በበጋና  በልግ ወቅቶች በቆሎ፣ ድንች፣ ጥቅል ጎመን፣ ቆስጣ፣ ቀይ ስር፣ ካሮት እና ሰላጣ  በስፋት ይለማሉ፡፡ በመኽር ወቅት ደግሞ ስንዴ ባቄላና ገብስ በዋናነት የሚለሙ ናቸው፡፡

ቦታው እንዳይሸረሸር ጠረጴዛማ እርከን ተሰርቶ የተለያዩ የተሻሻሉ የእንስሳት መኖዎችን በማልማት በስፋት ማስተማሪያ ሆኗል፡፡ እንዲሁም በጠረጴዛማው እርከን ላይ የለሙት እንደ ደሾ ሳር፣ የዝሆን ሳር እና ሌሎች የመኖ ዓይነቶች ማዕከሉን ልዩ ውበት አላብሰውታል፡፡

ዘጋቢ፡- ሸምሱዲን ዩሱፍ

ፎቶ፡- ማቲዎስ ተገኝ