በሀገራችን ባለፉት በርካታ ዓመታት የተፈጥሮ ዑደትን ባላማከለ መልኩ በነበረው የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ምክኒያት የብዝሃ-ሕይወት መመናመን፣ የመሬት መራቆትና መደህየት፣ የምርታማነት መቀነስ፣ የውሃ አካላት በደለል መሞላትና የመጠን መቀነስ እንዲሁም መጥፋት ማህበረሰባችንን ለከፋ ድርቅ፣ ለጎርፍና ለምግብ ዋስትና ችግሮች ተጋላጭ ከማድረጉም ባሻገር ለስደት እና ለመከራ ሲዳርግ ቆይቷል።

ይህንንም ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጭነት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የተፈጥሮ ሀብትን በመንከባከብ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ከመቋቋም ባለፈ እንደሀገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ግብ አስቀምጦ ላለፉት 7 ዓመታት ሲተገበር የቆየ ፕሮግራም ነው፡፡

ይህም መርሃ-ግብር ኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚን በመገንባት ከካርበን ልቀት ነጻ የሆነ ከባቢን በመፍጠር የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት በማሳደግ ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

ኢትዮጵያ ከአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በርካታ የሚቆጠር በረከቶችን አትርፋለች፡፡ በዚህም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የመንግሥትና የሕዝብ ቅንጅትን በላቀ ደረጃ እንዲታይ ትልቅ አቅም የፈጠረ መርሃ-ግብር ነው፡፡

መርሃ-ግብሩ ከተጀመረበት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ 48 ቢሊዮን ችግኞችን መትከል የተቻለ ሲሆን በዚህም 11 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በደን እንዲሸፈን አስችሏል፡፡

በ2010 ዓ.ም 17.2 በመቶ የነበረው የደን ሽፋናችን በ2016 ዓ.ም 23.6 በመቶ ከፍ እንዲል ከማስቻሉም ባለፈ የአፈር መሸርሸር መቀነስና የተጎዱ አካባቢዎች ማንሰራራት እንዲችሉ አድርጓል፡፡ የተለያዩ የውኃ አካላት መመለስና ማንሠራራት እንዲችሉም ትልቅ አስተዋፅዖ አበርክቷል፡፡

የአፈር መሸርሸርን በመቀነስ በየዓመቱ ወደ ወንዞች ታጥቦ ይገባ የነበረውን የአፈር ሀብት ከ2 ቢሊየን ቶን ወደ 208 ሚሊየን ቶን እንዲቀንስ ያደረገ ሲሆን የአፈር ለምነትን በመጨመር ምርታማነትን ማሳደግ አስችሏል።

በአረንጓ አሻራ መርሃ-ግብር በሁለቱም ምዕራፎች የተተከሉ ችግኞችን 56 ቢሊየን ለማድርስ ርብርብ እየተደረገ ሲሆን ይህም ተግባር ሀገራችን በዓለም ትልቁ ዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት ልማት መርሃ-ግብር የሚተገበርባት ሀገር እንድትሆን ሚናው የጎላ ነው፡፡
አጠቃላይ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ሃገራችን የተለያዩ አለማቀፍና አህጉር አቀፍ እውቅናዎችን እንድታገኝ ምክንያት ሆኗል፡፡

በዘንድሮው የ2018 የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር “ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ሃሳብ 8.5 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰኔ 8 ቀን 2018 ዓ.ም በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ ሐይቅ ዳርቻ በይፋ ማስጀመራቸው ይታወሳል።
አዘጋጅ፡- ሰለሞን ደምሰው
