FDRE Ministry of Agriculture

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ለግብርና ምርትና ምርታማነት ሚናውን እየተወጣ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6/2018(ግብርና ሚኒስቴር) የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የምግብ ስርዓትን በማሻሻል፤ ገበያን በማሳደግና ሥነ ምህዳርን በመመለስ ለግብርና ምርትና ምርታማነት ገንቢ ሚና እየተወጣ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር ኢያሱ ኤልያስ ገለጹ።

የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ጥምረት /አግራ/ የተመሰረተበትን 20ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የከፍተኛ ባለሙያዎችና የሥራ ሀላፊዎች ውይይት ተካሄዷል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር ኢያሱ ኤልያስ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በአፍሪካ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ዘላቂ ዕድገት ለማስመዝገብ የግብርና ሽግግር ወሳኝ ነው።

የግብርና ሽግግርን ለማረጋገጥ ደግሞ ለአርሶ አደሩ ዘላቂ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን መፍጠር ይገባል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ግብርና የአግሮ ፎረስትሪ ስትራቴጂ እና ሌሎች ኢንሼቲቮችን በመጀመር የምርት ስርዓቱ እንዲቀየር፣ የትራክተርና ኮምባይነር ግብዓት በዕጅጉ እንዲሻሻል መደረጉን ገልጸዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አካባቢን በመጠበቅ፣ ገበያን በማሳደግና የምግብ ስርዓትን በማሻሻል ለምርትና ምርታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገርና ቴክኖሎጂ የታጠቀ የግብርና ሥርዓት እየተገበረች መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ሽግግር በመፍጠር የገጠር ሽግግር፣ ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገትና የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ግብ ይዛ እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።

የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ጥምረት /አግራ/ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም በሚያስችሉ ስራዎች ላይ በማማከር፣ በመስኖ ልማትና የተሻሻለ ግብርና ላይ በማተኮር ለአነስተኛ አርሶ አደሮች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በጠንካራ አመራርና ውሳኔ ሰጭነት በግብርናው ዘርፍ ስኬት አስመዝግባለች ብለዋል።

በኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ተጨባጭ ውጤት መምጣቱን በመጥቀስ፤ አግራ ከመንግሥትና አጋር አካላት ጋር በመተባበር የድርሻውን ተወጥቷል ብለዋል።

የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ጥምረት /አግራ/ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ይሄነው ዘውዴ (ዶ/ር)፤ ባለፉት 20 ዓመታት ከኢትዮጵያ ጋር በጠንካራ ትብብር መስራታቸውን ገልጸዋል።

አግራ ጥምረት በመሆኑ በትብብር ያምናል ያሉት ዳይሬክተሩ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ባለሙያዎችን በማሰማራት ሲሰራ መቆየቱንም ተናግረዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

#ከማምረትበላይ #BeyondProduction