FDRE Ministry of Agriculture

የአለባ ዑደት ተኮር የኤክስቴን ዘዴ እና ተግባራዊ የወተት ከብቶች አያያዝ

የወተት ከብት አርቢዎች እያንዳንዱን የአለባ ደረጃ ተከትለው ለላሞች ተገቢውን እንክብካቤ ማድረግ የምግብና ሥነ-ምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ ባለፈ በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ ሊያደርጋቸው ይችላል።


የአለባ ዑደት ተኮር የኤክስቴን ዘዴ ጠቀሜታዎች

• የምርታማነት ጭማሪ፦ የአመጋገብና ምቾት አያያዝን በማሻሻል የወተት ምርትን በቀን ከ3–4 ሊትር ያሳድጋል።
• መኖ ብክነትን መቀነስ፦ ላሞችን እንደየአለባ ደረጃቸው በመመገብ አላስፈላጊ የመኖ ወጪን ያስቀራል።
• የጤናና ርቢ ብቃት ማሻሻል፦ የጡት በሽታን በመከላከል በወሊድ መካከል ያለውን ጊዜ ያሳጥራል።
• ከፍተኛ ትርፋማነት፦ ንቁና ጤነኛ ጥጆችን በማግኘትና የምርት ዘመንን በማራዘም ገቢን ያሳድጋል።

የአለባ ዑደት ደረጃዎች አተገባበር

ደረጃ 1. (መጀመሪያ አለባ)፡- ከወሊድ እስከ 100 ቀናት ያለው ጊዜ ሲሆን ይህም ላሟ ከፍተኛ ወተት የምትሰጥበትና ልዩ ጥንቃቄ የምትፈልግበት ወቅት ነው።

አመጋገብና ውሃ፦ ምጥን መኖ በ2 ኪ.ግ በመጀመር ለእያንዳንዱ 2 ሊትር ተጨማሪ ወተት 1 ኪ.ግ በመጨመር በቀን እስከ 10 ኪ.ግ መመገብ ነው። የድርቆ መኖ ከሰውነት ክብደቷ 3% መሆኑንና ንጹህ ውሃ በነፃነት ማግኘቷን ማረጋገጥ፤
ምቾትና ጤንነት፦ የምጥን መኖ በአንድ ምገባ ከ3 ኪ.ግ እንዳይበልጥና የግባስና ምጥን መኖ ጥምርታ 60፡40 መሆኑን ማረጋገጥ፤ መጠለያው ደረቅና ምቹ መሆን አለበት። የሰውነት ሁኔታ ነጥብ (BCS) ከ2.5-3 እንዳይያንስ መከታተል፤
ደረጃ 2. (መካከለኛ አለባ):- ከጸነሰች ጀምሮ እስከ 3 ወር እርግዝና ነው፡፡
ርቢና የሰውነት ሁኔታ፦ የድሪ ምልክትን በቅርበት በመከታተል በትክክለኛው ሰዓት ማስጠቃትና እርግዝናን ማረጋገጥ፤ የሰውነት አቋም ነጥብ ከ2.5 እስከ 3.5 እንዲሆን ማድረግ፤
መኖ ማስተካከያ፦ የወተት ምርቷ ሲቀንስ ለእያንዳንዱ 2 ሊትር ቅናሽ 1 ኪ.ግ ምጥን መኖ መቀነስ። ጥራቱን የጠበቀ ግባስ መኖ (Roughage) በነፃነት ማቅረብ፤
ደረጃ 3. (ማክተሚያ አለባ)፡- ከ3 ወር እርግዝና እስከ ወሊድ 45-60 ቀናት ሲቀራት
• አመጋገብ፦ በምትቀንሰው ለእያንዳንዱ 2 ሊትር ወተት 1 ኪ.ግ ምጥን መኖን በመቀነስ የግባስ መኖ በነፃነት ማቅረብ፤
• የመኖ ማስተካከያ፦ አለባ ስታቆም የሰውነት አቋም ነጥቧ (BCS) 3.5 እንዲሆን ታሳቢ በማድረግ ምጥን መኖ ማስተካከል፤
ደረጃ 4. (የማረፊያ ወቅት):- በአማካይ ከ45 እስከ 60 ቀናት
አለባ የማቆም ሂደት፦ የወተት ምርቷ በቀን ከ5 ሊትር በታች ሲሆን ማለብ ማቆም፤
አመጋገብና ምቾት፦ ዝቅተኛና ጥራት ያላቸውን ግባስ መኖዎችና የሰብል ተረፈ ምርቶችን ብቻ መመገብ። በዚህ ወቅት የፕሮቲን ምንጮችንና የኖራ ድንጋይ አለመመገብ ነው። በቂ እንቅስቃሴ ማድረጓንና ከጭንቀት ነፃ መሆኗን ማረጋገጥ ይገባል።
በአጠቃላይ እያንዳንዱን የአለባ ዑደት ደረጃ በአግባቡ መከታተልና የአመጋገብ፣ የጤና እና የምቾት አያያዝ መመሪያዎችን ተግባራዊ ማድረግ የወተት ምርታማነትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው፡፡


ምንጭ፡- ክእንሰሳትና ዓሣ ኤክስቴንሽን መሪ ሥራ አስፈጻሚ