FDRE Ministry of Agriculture

የኅብር ቀን ለህብረ-ብሄራዊ እና ለወል ትርክት ግንባታ!

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) በአዲስ አመት ለሁለንተናዊ ሀገራዊ ብልጽግና እና ለግብርናው ሽግግር ይበልጥ መነሳሳትን ለመፍጠር የግብርና ሚኒስቴር አመራሮችና ሰራተኞች የኅብር ቀንን አከበሩ፡፡

እለቱን በማስመልከት የመወያያ ሰነድ ያቀረቡት የግብርና ሚኒስትሩ አማካሪ ማርቆስ ሌራንጎ የኅብር ቀን ብዝኃነት የኢትዮጵያ ጌጥ መሆኑን በሚያረጋግጥ መልኩ በመላ አገሪቱ እተከበረ ነው ብለዋል፡፡

የብዝኃነት ጌጥ እርስ በእርስ በመረዳዳትና አንዳችን ለሌላችን ጥላና ከለላ በመሆን የሚገለፅ ሲሆን የመልክአ ምድር፣ የአመጋገብ፣ የአለባበስ፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖት፣ የፖለቲካዊ አመለካከትና ሌሎች ልዩነቶቻችን የኢትዮጵያ አቅሞች መሆናቸውን አቶ ማርቆስ ተናግረዋል፡፡

ኅብር ራስን ሆኖ በጋራ መኖር በመሆኑ የሃሳብ እና የፍላጎት ልዩነትን በመቻቻል፣ በመፈቃቀድና በመከባበር ላይ የተመሰረተ አብሮነት በማድረግ የወል ትርክት እና ኅብረ-ብሄራዊነትን መገንባት መሆኑን አማካሪው ገልፀው የኅብር ቀን አንድ ጊዜ ተከብሮ የሚያበቃ ሳይሆን በየቀኑ የሚከወን ባህል ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የኅብር ቀን የመረዳዳትና የመተባበር አንዱ መገለጫ በመሆኑ የግብርና ሚኒስቴር አመራሮችና ሰራተኞች ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የንፅህና መስጫ ቁሳቁስ፣ የምግብና አልባሳት፣ ቦርሳ እና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ ከሙያዊ ኃላፊነታቸው ባለፈ ለማህበራዊና ሰብዓዊ ኃላፊነት ድርሻቸውን ተወጥተዋል፡፡

ድጋፉ ከ4000 በላይ ለሚሆኑ በሆስፒታል የሚገኙ ህሙማንና አስታማሚዎች፣ በማዕከል የሚገኙ የአዕምሮ ህሙማን እና ወላጅ አልባ ህጻናት፣ በማዕከል ላሉ የካንሰር ታካሚ ህጻናት፣ ለችግር ለተጋለጡ ወላጅ አልባ ህጻናት እና ተማሪዎችን ተደራሽ ያደረገ ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን የደም ልገሳ ፕሮግራም ተከናውኗል፡፡