//////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////
መሬት በተንከባከብናት ልክ ከዛም አልፎ የልፋታችንን እጥፍ ትከፍላለች፡፡ በተቃራኒው እንክብካቤና ድጋፋችን በተጓደለ ቁጥር አበርክቶዋና ልግስናዋ በእጅጉ ይቀንሳል፡፡ በመሆኑም መሬትን በልዩ ሁኔታ ደግሞ የአፈር ለምነትና ጤንነትን መጠበቅ ለነገ የማይባል ዛሬ የሚከናወን የህልውና ተግባር ነው፡፡
የአፈር ለምነትና ጤንነትን መጠበቅ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን የሚያበረክት ሲሆን የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ በኢትዮጵያም ይሁን በሌሎች አገራት አፈር የግብርናው እንቅስቃሴ የሚካሄድበት ሰፊው አውድ ነው፡፡
የግብርናው ዘርፍ ዘላቂ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ዋነኛው የትኩረት መስክ ነው፡፡ የአፈር ለምነትና ጤንነትን በመጠበቅ ለግብርና ምቹ የሆነ አውድን መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ይህም በአስፈላጊ ንጥረ-ነገር የበለጸገ አፈር እንዲኖር በማድረግ የግብርናውን ምርታማነት በዘላቂነት ማሳደግ ያስችላል፡፡
የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የአፈር ለምነትና ጤንነትን መጠበቅ የውዴታ ግዴታ መሆኑን የተረዱት ታታሪው አርሶአደር ወደ ተግባራዊ ስራ ከገቡ ጥቂት አመታት ቢሆንም በአጭር ጊዜ ያገኙት ለውጥ ግን ሙሉ ትኩረታቸውን አፈርን መንከባከብ ላይ እንዲያደርጉ አስችሏቸዋል፡፡

አርሶአደር ሴማ አልባዞ ይባላሉ፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ዞን አበላ አበያ ወረዳ አበላሾያ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ ቀበሌው ዝናብ አጠር አካባቢ እንደመሆኑ የግብርና ምርታማነታቸውን ለማሳደግ የእቀባ እርሻ ቴክኖሎጂን እየተገበሩ ይገኛሉ፡፡
የእቀባ እርሻ ስራን በ2014 ዓ.ም እንደጀመሩ የሚናገሩት አርሶአደር ሴማ በመንግስት ስራ ተሰማርተው የነበሩና ለግብርና ስራ ልዩ ፍቅር ስላላቸው የአርሶአደርነት ሙያውን በሙሉ ልብ ተቀላቅለዋል፡፡
አርሶአደር ሴማ የእቀባ እርሻ ቴክኖሎጂ በቂ ውሃ በሌለበት እና አፈሩ ለፀሃይ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ፍቱን ቴክኖሎጂ መሆኑን በመረዳት እየሰሩበት ይገኛሉ፡፡ አሁን ላይ 1 ሄክታር መሬታቸውን የእቀባ እርሻ ቴክኖሎጂ በመጠቀም አረንጓዴ አልብሰውታል፡፡ ከአመት ወደ አመት የማሳቸው አፈር ለምነት እንዲጨምርም አድርገዋል፡፡
በእቀባ እርሻ ስራቸው የአፈር እርጥበቱን ለመጠበቅና ለምነቱን ለመጨመር ማሳቸውን በሚበሰብሱ የሳር፣ገለባና የሰብል ተረፈ-ምርት ከመሸፈናቸው ባለፈ የሰብል ማፈራረቅና ስብጥር ላይ ትኩረት አድርገው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
አትክልትና ፍራፍሬዎች እርጥበትን ይወዳሉ የሚሉት ታታሪው አርሶአደር አካባቢያቸው እርጥበት አጠር በመሆኑ ለዚህ ምቹ ቴክኖሎጂ የሆነውን የእቀባ እርሻ በመተግበራቸው ማሳቸውን የአትክልትና ፍራፍሬ መንደር አድርገውታል፡፡ ለዚህ እንዲረዳቸው ውሃን በቤተሰብ ገንዳ በመያዝ፣ የዝናብ ውሃን ወደ ማሳ በማስገባና የእቀባ ስራው ላይ በማሳረፍ መሬቱ እርጥበቱን ጠብቆ እስከሚቀጥለው የዝናብ ወቅት እንዲቆይ እያደረጉ ነው፡፡ ሰብሎችም የእርጥበት ችግር ሳይገጥማቸው ምርት እየሰጡ ነው፡፡ በእቀባ እርሻ ቴክኖሎጂው ምክንያት ምርታቸው በፊት ከነበረው በከፍተኛ መጠን ጨምሯል፡፡

በዚህም በኑሯቸው ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት የቻሉ ሲሆን ለአጎራባችና ሌሎች አርሶአደሮች ተሞክሯቸውን እያካፈሉና ከሌሎችም እየተማሩ ይገኛሉ፡፡ መሬት በተንከባከብካት ልክ ትከፍልሃለች የሚሉት አርሶአደር ሴማ ጠዋት ማታ በማሳ ቦታ በመገኘት ከመሬት የሚገባንን ነገር ለማግኘት ለመሬት ቅድሚያ የሚገባትን መስጠት አለብን ብለው ለተግባራዊነቱ እየሰሩ ነው፡፡ የእቀባ እርሻ ቴክኖሎጂ ተሞክሮውን ወደ ሌሎች በማስፋት እርጥበት አጠር በሆኑ አካባቢዎች የሚታየውን የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትን በመከላከል አርሶአደሩ ኑሮውን እንዲያሻሽል ያስችላል ሲሉ ሃሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡
