አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) በኢትዮጵያ ያለውን የግብርና ኢንቨስትመንት አጠቃላይ ሁኔታ ለመገምገም፣ የቴክኖሎጂ አቅርቦትን ለማሳለጥ እና የፋይናንስ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ያለመ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የምክክርና የሥልጠና መድረክ ዛሬ ተጀምሯል።

የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) በርካታ አርሶአደሮች ሕይወታቸውን በመቀየር ወደ ባለሀብትነት እየተሻገሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ይህን ስኬት ዘላቂ ለማድረግ የግብርና ኢንቨስትመንትን ከምርምር ሥራዎች ጋር ማስተሳሰር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶችም በአቅራቢያቸው የሚገኙ አርሶአደሮችን በቴክኖሎጂና በዕውቀት ማገዝ እንዳለባቸው ዶ/ር ሶፊያ አሳስበዋል።

በጀርመን መንግሥት በሚደገፈው ኃላፊነት የተሞላበት የግብርና ኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ተወካይ ክሪስቲያን መስመር በግብርናው ክፍለ-ኢኮኖሚ ለተሰማሩ የግሉ ዘርፍ አልሚ ባለሀብቶች የሚቀርቡ ማበረታቻዎች ከተጠናከረ የድጋፍና የቁጥጥር ሥርዓት ጋር ማጣመር ኢንቨስትመንቱን ዘላቂና ውጤታማ እንዲሆን የሚያስችል ወሳኝ አካሄድ እንደሆነ አስገንዝበዋል።

በመድረኩም ወቅታዊ የግብርና ኢንቨስትመንት ገጽታና ቀጣይ አቅጣጫዎች እንዲሁም በቴክኖሎጂዎችና አዳዲስ አሰራሮች ዙሪያ እና ሌሎች ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት የተደረገ ሲሆን መድረኩ ለሁለት ቀናት የሚቀጥል ይሆናል፡፡

ዘጋቢ፦ ጌዲዮን ነጋሽ
