ቴምር በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ረጅም ዘመናትን የተሻገረ፣ ለምግብነት እና ለማህበራዊ ህይወት ከፍተኛ ዋጋ ያለው ድንቅ የተፈጥሮ ስጦታ ነው።
በርካታ የታሪክ መዛግብት እና መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የቴምር ዛፍ እርሻ የተጀመረው ከአምስት ሺህ ዓመታት በፊት በመካከለኛው ምስራቅ እና በሜሶፖታሚያ የአሁኗ ኢራቅ አካባቢ ነበር።
በበረሃማ እና ሞቃታማ የአየር ፀባይ ውስጥ በፅናት የማደግ ተፈጥሯዊ ሚስጥርን የያዘው ቴምር ጥንታውያኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ለረጅም መንገድ ጉዞዎች እና ለድርቅ ጊዜያት እንደ ዋና የምግብ ምንጭ እንዲጠቀሙበት አስችሏቸዋል።
ረጅም ጊዜ የመቆየት ባህሪውም በንግድ መስመሮች በኩል በፍጥነት ወደ ተለያዩ የዓለም ክፍሎች እንዲሰራጭ አድርጎታል።
በአለም አቀፍ ደረጃ የቴምር ምርት እና ንግድ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚታይበት ዘርፍ ሲሆን በአሁኑ ወቅት እንደ ግብፅ፣ ሳውዲ አረቢያ፣ ኢራን፣ አልጄሪያ እና ኢራቅ ያሉ ሀገራት ከፍተኛውን የቴምር ምርት ለዓለም ገበያ የሚያቀርቡ ዋና ዋና አምራቾች ሲሆኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ቴምር ወደ ተለያዩ የዓለም ክፍሎች እየተስፋፋ መጥቷል።
ለዚህም ዋናው ምክንያት የቴምር ከፍተኛ የጤና አወንታዊ ጎኖች፣ ማለትም በተፈጥሯዊ ስኳር፣ በፋይበር፣ በቪታሚኖች እና በማዕድናት የበለፀገ መሆኑ ነው። ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ የቴምርን ገበያ እያሰፋው ይገኛል።

ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ ስንመጣ፣ ሀገሪቱ ለቴምር ልማት እጅግ በጣም ምቹ የሆነ የተፈጥሮ አየር ጠባይ እና የመሬት ሀብት አላት።
በተለይም እንደ አፋር፣ ሶማሌ፣ ድሬዳዋ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በታችኛው ኦሞ ሸለቆ ያሉ ዝቅተኛ እና ሞቃታማ (ቆላማ) አካባቢዎች ለቴምር ዛፍ እድገትና ምርታማነት ተስማሚ ናቸው።
ከዚህ ጋር በተያያዘም በሀገራችን በተለይም በአፋር ክልል ከ500 እስከ 700 ሺህ ሄክታር መሬት ለቴምር ልማት ምቹ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በክልሉ ከ453 ሄክታር መሬት በቴምር እየለማ ይገኛል፡፡
የከርሰ ምድር ውሃ እና የወንዞች ፍሰት ባላቸው በእነዚህ አካባቢዎች ቴምርን በሰፊው በማልማት ሀገሪቱ ከውጭ የምታስገባውን ምርት በሀገር ውስጥ መተካት ይቻላል።
በኢትዮጵያ ያለውን የተፈጥሮ ምቹ ሁኔታ በበቂ ሁኔታ በመጠቀም የቴምር ምርትን በማሳደግ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡
በቆላማ አካባቢዎች ለሚኖሩ አርብቶ አደሮች እና ከፊል አርብቶ አደሮች የገቢ ምንጭ ከመፍጠሩም በላይ፣ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ይፈጥራል። ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት ለቴምር የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ ለማዳን እና በቀጣይም ምርቱን ወደ ጎረቤት ሀገራት በመላክ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ትልቅ እድል ይፈጥራል፡፡
በዚህም በምርምር የተደገፉ የቴምር ዝርያዎችን በማስተዋወቅና በማስፋፋት፣ አምራቹን ማህበረሰብ በማሰልጠን እና የኢንቨስትመንት ድጋፍ በማድረግ ዘርፉን ማጠናከር ለሀገር እድገት ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል።
ሁለተኛው አለምአቀፍ የቴምር ፌስቲቫል በኢትዮጵያ አዘጋጅነት ከመስከረም 10 እስከ 12/2019 ዓ.ም በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ በተለያዩ ሁነቶች ይከበራል።
አዘጋጅ፡- ሰለሞን ደምሰው
