——————————–
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የም ዞን ደሪ ሳጃ ዙሪያ ወረዳ የዲቻ ቀበሌ አርሶአደሮች ስራ-አጥ ወጣቶች ከተለያዩ የገጠር ቀበሌዎች ተመልምለው በ2012 ዓ.ም የሰፈሩ ናቸው፡፡
ወጣቶቹ የሰፈሩት አካባቢ ሸለቆኣማ ሆኖ ዝቅተኛ እና ሞቃታማ ከመሆኑም ባሻገር መሰረተ ልማት የሌለው ጫካ ነበር፡፡ ነገር ግን አካባቢው በለም አፈር፣ በውሃ ሀብት እና ለተለያዩ የሰብል ዓይነቶችና ፍራፍሬዎች ልማት ተስማሚ በመሆኑ በተፈጥሮ ፀጋ የታደለ ነው፡፡
በዲቻ ቀበሌ ከሰፈሩት 600 ወጣቶች ውስጥ ዛሬ አካባቢውን እያለሙ ያሉት 250 ብቻ ናቸው፡፡ 350 ወጣቶች ሙቀቱንና ጊዜያዊ ችግሮችን መታገስ ተስኗቸው ለቀዋል፡፡
ጊደር ያለው አርሶአደር ጊዜያዊ ችግሮችን በትዕግስት አሳልፎ የጊደሯን ወተት እንደሚጠጣ ሁሉ ታግሰው ጊዜያዊ ችግሮችን የተቋቋሙ ወጣቶችም አካባቢውን አልምተው ፍሬውን በማጣጣም “ታጋሽ የጊደር ወተት ይጠጣል” የሚለውን አባባል እውን አድርገዋል፡፡

የአካባቢውን ፀጋ ተገንዝበው ተስፋን ሰንቀው ችግሮችን ሁሉ በመቋቋም በቁርጠኝነት ወደ ልማት የገቡት ወጣቶች በመንግስት ድጋፍ በዋናነት ማሽላ፣ በቆሎ፣ ሙዝ እና ፓፓያ ነበር ማልማት የጀመሩት፡፡
ውጤቱ ሲታይ አካባቢው ለሙዝና ለፓፓያ እጅግ ተስማሚ በመሆኑ ወጣቶቹ በ30-40-30 ኢኒሼቲቭ መሰረት በኩታ-ገጠም እርሻ (በክላስተር) ተደራጅተው ሙዝ እና ፓፓያን በማልማት ተምሳሌት መሆን ችለዋል፡፡
በ2014 ዓ.ም በሙዝ ክላስተር ላይ የተደራጁት 11 ወጣት አርሶአደሮች ናቸው፡፡ በ7.5 ሄክታር ጀምረው በየዓመቱ እየተከሉ በክላስተር የሚያለሙትን የሙዝ እርሻን 11 ሄክታር አድርሰዋል፡፡

ተደራጅተው በክላስተር ሙዝን እያለሙ ካሉት አርሶአደሮች መካከል አርሶአደር ዘመዴ ካሳዬ አንዱ ነው፡፡ አርሶአድር ዘመዴ እንደነገረን፣ በክላስተር እየለማ ካለው 11 ሄክታር መሬት ውስጥ 2 ሄክታር የሱ ነው፡፡
በ2017 ዓ.ም በክላስተር ከለማው ሙዝ ብቻ 200 ሺህ ብር ገቢ አግኝቷል፡፡ ከዚው ገቢ 1 ሞተር ሳይክል በ150 ሺህ ብር የገዛ ሲሆን ከዚህም እራሱ ሲሰራበት ከነዳጅ ወጪ ቀሪ በቀን 1000 ብር ገቢ ያገኛል፡፡ በሳጃ ከተማ ቤት ለመስራትም 300 ካሬ ሜትር መሬት ገዝቷል፡፡

አርሶአደር ዘመዴ በክላስተር ከሚያለማው ሙዝ ውጪም ማሽላ፣ በቆሎ እንዲሁም ሙዝን ጨምሮ የተለያዩ ፍራፍሬዎችን ያለማል፡፡ ወደፊት የግብርና ስራን ማስፋፋትና በአካባቢው የእህል ወፍጮ በመትከል የማህበረሰቡን ችግር ለማቃለል እቅድ አለው፡፡
ሌላው በ2.5 ሄክታር መሬት ላይ በ6 አባላት እየለማ ያለው የፓፓያ ክላስተር ነው፡፡ የክላስተር ቡድኑ ስም ያኒ ወሰተረ ዲችኒ (ኑ አብረን ሰርተን እንደግ) ይባላል፡፡ እውነትም የክላስተር ቡድኑ አባላት አብረው አያደጉ ይገኛሉ፡፡

አርሶአደር አጥናፉ ወልደየሱስ የፓፓያ ክላስተር ቡድን ሳብሳቢ ነው፡፡ አርሶአደር አጥናፉ እንደነገረን መሬቱን ሳይከፋፈሉ ስድስቱም አባላት በጋራ አልምተው፣ በጋራ አምርተው፣ ገቢውንም በጋራ የባንክ ሂሳብ ደብተር ይቆጥባሉ፡፡
የፓፓያ ክላስተር ቡድን አባላት ከፓፓያ ልማት ጎን ለጎን ዓሳና ዶሮ በማርባት የተቀናጀ ግብርናን እየተገበሩ ይገኛሉ፡፡ እስከ አሁን ከፓፓያ ምርት ገቢ ብቻ 400 ሺህ ብር ቆጥበዋል፡፡ ወደፊትም የጋራ ስራቸውን አጠናክረው በመቀጠል በጋራ ለማደግ እቅድ አላቸው፡፡
የፓፓያ ክላስተር ቡድን አባላት በግላቸው በተሰጣቸው መሬት ላይ ደግሞ የተለያዩ ሰብሎችና ፍራፍሬዎችን በማልማት ጥሩ ኑሮ እየኖሩ ነው፡፡

ከገበያ ጋር ተያይዞ ከደላላዎች ጣልቃ-ገብነት ነፃ የሆነ የገበያ ትስስር ለመፍጠር በክልሉ የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም በጀት ድጋፍ የአትክልትና ፍራፍሬ ገበያ ማዕከል በሳጃ ከተማ ተገንብቷል፡፡
ገበያ ማዕከሉ በ40 ሚሊዮን ብር የተገነባ ሲሆን እንደክልሉም ልምድ የሚወሰድበት ነው፡፡ ገበያ ማዕከሉ ስራ ሲጀምር እስከ ማዕከላዊ ገበያ (አዲስ አበባ) ድረስ ምርቱ ሊቀርብ ይችላል፡፡
ከአርሶአደሮቹ ስኬት ጅርባ ያለው የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ነው፡፡ በጣም ውድ የሆኑ የተሻሻሉ የሙዝና የፓፓያ ዝሪያዎችን በማቅረብ የማይተካ ሚና ተጫውቷል፡፡
በዞኑ ግብርና መምሪያ የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ዳዊት ገ/ሥላሴ እንደ ገለፁት፣ ፕሮግራሙ እስከ አሁን ለዲቻ ቀበሌ ብቻ 3.5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡ ፕሮግራሙ በ2017 ዓ.ም 3.5 የፓፓያ ምርጥ ዝሪያ እንዲተከል ያደረገ ሲሆን በ2018 ዓ.ም ደግሞ ለማስፋት ከወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው፡፡

አዘጋጅ፡- ሸምሱዲን ዩሱፍ
ፎቶግራፈር፡- ዮዲት እንዳለው
