ባለፉት በርካታ ዓመታት በሀገራችን የነበረው የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም እንዲሁም ዘርፉ በወቅቱ ትኩረት ባለመሰጠቱ ምክንያት በቢሊዮን ቶን የሚለካ ለም የአፈር ሀብታችን እየታጠበ ወደ ጎረቤት ሀገራት ሲወጣ ቆይቷል።

በሀገራችን ለእርሻ ስራ ከሚታረሰው መሬት ውስጥ በዓመት እስከ 130 ቶን አፈር በሄክታር፣ ከባዶ መሬት ላይ እስከ 300 ቶን አፈር በሄክታር በየዓመቱ እንደሚሸረሸር የተለያዩ ጥናቶች ያመላክታሉ።

በዚህም ከ50 ሚሊየን ሄክታር በላይ የሆነ መሬት ደህይቶ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ መስጠት እንዳይችል ሆኗል። ይህ ደግሞ በሃገራችን የግብርና ምርት እና ምርታማነት ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ በማሳረፍ ዜጎችን ለምግብ ዋስትና ችግር እንዲጋለጡ ብሎም ለስደት እና ለመከራ ሲዳርግ የቆየ ማነቆ ነው።

ይህንን ችግር ለመቀልበስ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ ነገር ግን ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ስራ የገባው አሳታፊ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት እንቅስቃሴ ዜጎችን በተጎዱ ተፋሰሶች ላይ ከዳር እስከ ዳር በየዓመቱ በአማካይ 14 ሚሊየን የሚጠጋ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማነቃነቅ የተለያዩ ስነ-አካላዊ እና ስነ-ሕይወታዊ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን በመስራት አሁን ላይ በተለያየ መልኩ ሊገለጽ የሚችል ለውጥ ማምጣት ተችሏል፡፡

ባለፉት አስርት ዓመታት በመደበኛ የማህበረሰብ የተፋሰስ ንቅናቄ እና በተለያዩ ፕሮግራም እና ፕሮጀክቶች በተሰሩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች ተሸርሽረው ከተጎዱ ቦታዎች ውስጥ 33 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታሩን ማልማት ተችሏል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ባለፉት የለውጥ ዓመታት መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት አማካኝነት ተፋሰሶችን በተቀናጀ መንገድ በማልማት በተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የተለያዩ የውሃ ምንጮች እንዲጎለብቱ ከማስቻሉም ባሻገር የየአካባቢው ማህበረሰብ በተለይም ወጣቱን የህብረተሰብ ክፍል በማደራጀት በእንስሳት ማድለብ፣ በንብ ማነብ፣ በፍራፍሬ ልማት እንዲሁም በሌሎች የልማት መስኮች ላይ ተሳትፈው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ትልቅ አስተዋፅዖ እያበረከተ ይገኛል፡፡

በዘንድሮው ዓመትም በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ ከ4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት የታቀደ ሲሆን በ2017 በጀት ዓመት የተሰሩ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራዎችን የማደስ ስራም ትኩረት ተደርጎባቸዋል፡፡
በየአመቱ እንደየክልሎቹ ተጨባጭ ሁኔታ ከ30 እስከ 60 ቀናት አርሶአደሮችና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በየተፋሰሱ እየወጡ የተለያዩ የስነ-አካላዊ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን ያከናውናሉ፡፡

ይህንንም ዕቅድ ለማሳካት በሃገር አቀፍ ደረጃ ክልሎች የቅድመ-ዝግጅት ስራዎቻቸውን በማጠናቀቅ ወደ ስራ ገብተዋል፡፡
አዘጋጅ፡- ሰለሞን ደምሰው