አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስትቲዩትና በአካቴክ ቴክኖሎጂ አስተባባሪነት የአርሶአደሮችና ተያያዥ መረጃዎች አስተዳደር ማዕቀፍ ላይ የባለድርሻ አካላት ውይይት ተደርጓል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የፖሊሲና ስትራቴጂ ጥናትና ምርምር መሪ ስራ አስፈጻሚ ተስፋዬ መንግስቴ (ዶ/ር) የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲን ውጤታማ ለማድረግ የዘመነ የመረጃ ስርዓት መኖር ጥሩ መደላድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

የመረጃ ስርዓቱ እንደመነሻነት ከዚህ በፊት ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ድረስ በመረጃ ልውውጥ ላይ ሲደረግ የነበረውን አካሄድ ለማዘመን እንደሚያግዝ ጠቅሰው የአርሶ አደሮች ግለታሪክ የመረጃ ስርዓት ወደ መሬት ወርዶ ስራ ላይ እንዲውል የግብርና ሚኒስቴር በባለቤትነት ይከታተላል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስትቲዩት የዲጅታል ግብርና ዳይሬክተር ግሩም ከተማ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያ ወደ ዲጅታል ኢኮኖሚ ለምታደርገው ሽግግር የዘመነ የአርሶ አደር ግለታሪክ የመረጃ ስርዓት መኖር ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በመድረኩም የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ግለታሪክ መረጃ አያያዝ የጥናት ውጤት የቀረበ ሲሆን ሁሉንም መረጃ ወደ አንድ በማምጣት የአርሶ አደሩን ግለታሪክ መያዝ በመረጃ አያያዝ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታትና የመረጃ ስርዓቱን ለማዘመን እንደሚረዳ በጥናቱ ተመላክቷል፡፡
ዘጋቢ፡- ካሳሁን ማለቶ
ፎቶ፡- ጌታቸው ምትኩ
