አምቦ፣ ግንቦት 29/2018 ዓ.ም (ግብርና ሚኒስቴር) በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት መኖ ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ ከኦሮሚያ ክልል ለተውጣጡ ባለሙያዎች በተሻሻለ የመኖ ልማት ላይ በንድፈ-ሀሳብ እና በተግባር የተደገፈ የአሰልጣኞች ስልጠና ሰጥቷል፡፡

ስልጠናው በዋናነት በተሻሻሉ የመኖ አመራረት፣ አዘገጃጀት፣ አያያዝ እና አመጋገብ፣ በመኖ ዘር ብዜት እና በአፈር አልባ የአረንጓዴ መኖ ልማት ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡

የተሻሻሉ የመኖ እጽዋት በሳይንሳዊ ምርምር የተገኙ በዝርያቸው፣ በንጥረ ምግብ ይዘታቸውና በምርታማነታቸው ከፍተኛ የሆኑና ሀገር በቀል እና ከውጪ የሚገቡ ሲሆኑ ከሌሎች የመኖ እጽዋት በተሻለ የአካባቢውን የተፈጥሮ ሚዛን በመጠበቅ ጥራት ያለውን የእንስሳት ምርትና ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳድጉ ናቸው፡፡

የተሻሻለ የመኖ እጸዋት በተራቆቱና ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች መልማት የሚችል ሲሆን ከእንስሳት ንክኪ ነጻ በማድረግ በተተከለበት ማሳ ላይ በተደጋጋሚ በመልማት የመኖ ምርትና ምርታማነትን እንደሚጨምርና መደበኛ የእንስሳት መኖ ምርትን ከ3 እጥፍ በላይ ማሳደግ የሚችል መሆኑ በስልጠናው ወቅት ተጠቅሰዋል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ አማካሪ ደጀኔ ታከለ የእንስሳት መኖ ከመኖነት ባለፈ በምግብ እራስን ለመቻል ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቅሰው፣ የተሸሻለ የመኖ እጽዋት ምርትን ማስፋፋት በእንሳት ልማት ዘርፍ ውስጥ ወቅቱ የሚጠይቀው ወሳኝ ምዕራፍ ነው ብለዋል፡፡

የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭን ለመሳካት በተሰሩት የመኖ ልማት ስራዎች በእንስሳት ምርትና ምርታማነት ላይ አመርቂ ውጤት መመዝገቡንም ተናግረዋል።
በግብርና ሚኒስቴር የመኖ ሃብት ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ ሙሉጌታ ጉዲሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው የተሻሻለ የመኖ እጽዋት ጥራትን በማስጠበቅ የምግብ ዋስትናን እና የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ እንደሚቻል ገልፀዋል፡፡
ሀገራችን በእንስሳት ዘርፍ ያላትን የመጀመሪያ ደረጃን ማስቀጠል የምንችለው የተሸሻለ መኖን በመጠቀም የሚገኘውን የእንስሳት ተዋፅኦ በጥራትና በመጠን ማሳደግ ስንችል ነው ያሉት መሪ ስራ አስፈጻሚው፣ ይህንንም ለማሳካት ሰልጣኞቹ በንድፈ-ሀሳብ እና በተግባር የቀሰሙትን ትምህርት ወደታች በማውረድ በአግባቡ ተግባራዊ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡

በመጨረሻም በኦሮሚያ ክልል ከምዕራብ ዞኖች ለተውጣጡ የመኖ ሃብት ልማት ባለሙያዎች በአምቦ ከተማ ሲሰጥ የቆየው የአሰልጣኞች ስልጠና የተጠናቀቀ ሲሆን ቀጣዩ ስልጠና በሻሸመኔ ከተማ ይሰጣል፡፡
ዘጋቢ፡- ራቢያ ፋንታው
ፎቶ፡- ጌታቸው ምትኩ
